የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 26:1-11

ትንቢተ ኢሳይያስ 26:1-11 መቅካእኤ

በዚያም ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፦ የጸናች ከተማ አለችን፤ ቅጥሯንና ምሽጓን ለደኅንነታችን አኑሮታል። በእምነቱ የጸና ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ። በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ በአንተ ላይ ታምናለችና በሰላም ትጠብቃታለህ። ጌታ እግዚአብሔር የዘለዓለም ዐለት ነውና ለዘለዓለም በጌታ ታመኑ። በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፥ እስከ ትቢያም ድረስ ይጥላታል። እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም ኮቴ፥ ትረግጣታለች። የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንክ የጻድቃንን መንገድ ታቀናለህ። አቤቱ ጌታ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው። ፍርድህን በምድር ላይ በፈረድክ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች። ክፉዎች እድል ቢሰጣቸው እንኳን ጽድቅን አይማሩም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋሉ፥ የጌታንም ግርማ አያዩም። አቤቱ ጌታ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች።