ትንቢተ ኢሳይያስ 14
14
1ጌታ ግን ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተሳሰራል። 2አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ።
የባቢሎን ንጉሥ ውድቀት
3በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ፦ አስጨናቂ እንዴት አበቃለት! አስገባሪነቱስ እንዴት አከተመ! 5ጌታ የክፉዎችን ዘንግ፥ የገዢዎችንም በትረ መንግሥት ሰብሯል። 6ሕዝቦችንም በማያቋርጥ ቁጣ የመታውን፥ ያለ ርኅራኄ ያለማቋረጥ ቀጥቅጦ አሕዛብን በማይበርድ ቁጣው የገዛውን ሰብሮአል። 7ምድርም ሁሉ አርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። 8ጥድና የሊባኖስ ዝግባ፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። 9ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፥ የምድርንም ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። 10እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? 11ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። 12#ራእ. 8፥10፤ 9፥1።አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴትስ ወደ ምድር ተጣልክ! 13#ማቴ. 11፥23፤ ሉቃ. 10፥15።አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ 14ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። 16የሚያዩህ ይመለከቱሃልና፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17ዓለሙን ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልላከ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። 18የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጉድጓዱ ድንጋዮች የወረዱ ከድነውሃል፤ እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። 20ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘለዓለም የተጠራ አይሆንም። 21እንዳይነሱም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። 22በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል ጌታ። 23የጃርት መኖርያ የውሃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 24#ኢሳ. 10፥5-34፤ ናሆም 1፥1—3፥19፤ ሶፎ. 2፥13-15።የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ምሏል፦ “እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንዳሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። 25አሦርን በምድሬ ላይ እሰብራለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሳል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። 26በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት።”
በፍልስጤማዊያን ላይ የተነገረ ትንቢት
27የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው? 28#2ነገ. 16፥20፤ 2ዜ.መ. 28፥27።ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዘመን ይህ ሸክም ሆነ። 29#ኤር. 47፥1-7፤ ሕዝ. 25፥15-17፤ ኢዮብ 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥6-8፤ ሶፎ. 2፥4-7፤ ዘካ. 9፥5-7።ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30የድሆችም የበኩር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። 31አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል፥ አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። 32ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መልስ ይሰጣል? “ጌታ ጽዮንን መሥርቷል፥ ከሕዝቡም ችግረኞች በእርሷ ውስጥ መጠጊያን ያገኛሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ