ወደ ዕብራውያን 10:26-39

ወደ ዕብራውያን 10:26-39 መቅካእኤ

የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርብልንም፤ ነገር ግን የሚያስፈራ የፍርድና ተቃዋሚዎችንም ለመብላት የሚጠብቅ የእሳት ግለት አለ። የሙሴን ሕግ የተላለፈ ሰው “በሁለት እና በሦስት ምስክሮች ምስክርነት” ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ የተቀደሰበትን ያንን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያስቆጣ፥ ቅጣቱ እጅግ የከፋ እንዴት የማይሆን ይመስላችኋል? “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤” ያለውን እናውቃለን፤ ደግሞም “ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።” በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁባቸውን እነዚያን የመከራ ቀናት አስታውሱ፤ አንዳንድ ጊዜ በግላጭ ለነቀፋና ለስደት የተዳረጋችሁ ነበራችሁ፤ አንዳንዴም እንዲህ ካሉት ጋር በሚደርስባቸው ነገር ተካፋይ ሆናችሁ ነበር፤ በሰማይ የበለጠና ፍጻሜ የሌለው ሀብት እንዳላችሁ በማወቃችሁ፥ የንብረታችሁን መነጠቅ በደስታ ተቀበላችሁ፤ በእስራት ላይ የነበሩትን የስቃያቸው ተካፋይ ሆናችሁ። ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ ጽናት ያስፈልጋችኋል። ምክንያቱም ገና “በጣም ጥቂት ጊዜ፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል፥ አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ ነፍሴ ወደ ኋላም በሚያፈገፍግ በእርሱ ደስ አትሰኝም።” እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ጋር ነን እንጂ፥ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ጋር አይደለንም።