የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን 10

10
1ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጣው መልካም ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን ጥላ በመሆኑ፥ እውነተኛ አካል አይደለም። በየዓመቱም ዘወትር በሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚቀርቡትን ለፍጽምና ሊያበቃ ከቶ አይችልም። 2እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን ባቆሙ አልነበረምን? 3ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት ዓመታዊ የኃጢአት መታሰቢያ ነው ያለው፤ 4የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ለማስወገድ አይችልም።
5 # መዝ. 39፥7-9። በዚህ ምክንያት፥ ወደ ዓለም ሲመጣ፥
“መሥዋዕትንና መባን አልወደድክም፤
ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤
6በሚቃጠልና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት፥
አንተ ደስ አላለህም።
7በዚያን ጊዜ፥ ‘እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥
አምላኬ ሆይ! ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፥’ አልኩ፤”
ይላል። 8በዚህ ላይ “መሥዋዕትንና መባን የሚቃጠል መሥዋዕትንም፥ ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም፤” ይላል። እነዚህም እንደ ሕጉ የሚቀርቡት ናቸው። 9ከዚያም “እነሆ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ፤” ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። 10በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማቅረብ ተቀድሰናል።
11 # ዘፀ. 29፥38። ሊቀ ካህናትም ሁሉ በየዕለቱ እያገለገለ እነዚያን ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ደጋግሞ ለማቅረብ ይቆማል፤ 12#መዝ. 109፥1።እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድ መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ 13አሁን ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። 14ምክንያቱም አንድ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። 15መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ እንዲህ በማለት፦
16 # 8፥10፤ ኤር. 31፥33። “ከነዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፥ ይላል ጌታ፤
“በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ፥
በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ፤”
17 # 8፥12፤ ኤር. 31፥34። እንደዚሁም፥ “ኀጢአታቸውንና ዐመጻቸውንም ደግሜ አላስብም፤” ይላል። 18የእነዚህም ስርየት ባለበት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የለም።
ምክርና ተግሣጽ
19እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ ቅድስት ለመግባት በኢየሱስ ደም ድፍረት ስላለን፥ 20በአዲስና በሕያው መንገድ በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል ተከፍቶልን፥ 21በእግዚአብሔርም ቤት ላይ ታላቅ ካህን ስላለን፥ 22#ዘሌ. 8፥30፤ ሕዝ. 36፥25።ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተንና ሰውነታችንን በንጹህ ውሃ ታጥበን፥ በቅን ልብ በፍጹም እምነት እንቅረብ፤ 23የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና፥ ተስፋ የሚሰጠንን ምስክርነት ያለመናወጥ በጽናት እንጠብቅ፤ 24ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተሳሰብ፤ 25አንዳንዶችም ልምድ አድርገው እንደያዙት፥ መሰብሰባችንን አንተው፤ እርስ በርሳችን እንመካከር፤ ይልቁንም የቀኑን መቅረብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።
26የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርብልንም፤ 27#ኢሳ. 26፥11።ነገር ግን የሚያስፈራ የፍርድና ተቃዋሚዎችንም ለመብላት የሚጠብቅ የእሳት ግለት አለ። 28#ዘዳ. 17፥6፤ 19፥15።የሙሴን ሕግ የተላለፈ ሰው “በሁለት እና በሦስት ምስክሮች ምስክርነት” ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ 29#ዘፀ. 24፥8።እንግዲህ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፥ የተቀደሰበትን ያንን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ፥ የጸጋውንም መንፈስ ያስቆጣ፥ ቅጣቱ እጅግ የከፋ እንዴት የማይሆን ይመስላችኋል? 30#ዘዳ. 32፥35፤ ዘዳ. 32፥36።“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤” ያለውን እናውቃለን፤ ደግሞም “ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።” 31በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።
32ነገር ግን ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁባቸውን እነዚያን የመከራ ቀናት አስታውሱ፤ 33አንዳንድ ጊዜ በግላጭ ለነቀፋና ለስደት የተዳረጋችሁ ነበራችሁ፤ አንዳንዴም እንዲህ ካሉት ጋር በሚደርስባቸው ነገር ተካፋይ ሆናችሁ ነበር፤ 34በሰማይ የበለጠና ፍጻሜ የሌለው ሀብት እንዳላችሁ በማወቃችሁ፥ የንብረታችሁን መነጠቅ በደስታ ተቀበላችሁ፤ በእስራት ላይ የነበሩትን የስቃያቸው ተካፋይ ሆናችሁ። 35ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። 36የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ ጽናት ያስፈልጋችኋል።
37 # ዕን. 2፥3፤4። ምክንያቱም ገና “በጣም ጥቂት ጊዜ፥
ሊመጣ ያለውም ይመጣል፥ አይዘገይምም፤
38ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤
ነፍሴ ወደ ኋላም በሚያፈገፍግ በእርሱ ደስ አትሰኝም።”
39እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑት ጋር ነን እንጂ፥ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ ጋር አይደለንም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ