እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ፦ “እነዚህ እነማን ናቸው?” አለው። ዮሴፍም ለአባቱ፦ “እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው” አለ። እርሱም፦ “እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ” አለ። የእስራኤልም ዐይኖች ከሽምግልና የተነሣ ደክመው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም። እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፥ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ” አለው። ዮሴፍም ከጉልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ። ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፥ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኩር ነበርና። ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፥ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፥ በምድርም መካከል ይብዙ።” ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፥ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። ዮሴፍም አባቱን፦ “አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኩሩ ይህ ነውና፥ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ” አለው። አባቱም እንዲህ ሲል እንቢታውን ገለጸ፦ “አውቄአለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቄአለሁ፥ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፥ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።”
ኦሪት ዘፍጥረት 48 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 48:8-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች