የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 48:8-19

ዘፍጥረት 48:8-19 NASV

እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ። ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት። እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ። በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው። እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጕልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተቀኝ፣ ከእስራኤል በስተግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተግራ፣ ከእስራኤል በስተቀኝ በኩል አቀረባቸው። እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፤ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኵሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤ “አባቶቼ አብርሃምና ይሥሐቅ በፊቱ የተመላለሱት እግዚአብሔር፣ ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ፣ ከጕዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይሥሐቅ ስም ይጠሩ፤ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።” ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህኛው ስለ ሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እንቢ አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}