ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “ወደ ግብጽ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፥ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ። ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፥ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።” ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት፥ እርሱም፦ “እኅቴ ናት” አለ፥ የዚያም ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፥ እርሷ ውብ ነበረችና። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ እንዲህም አለው፦ “እነሆ ሚስትህ ናት፥ እንዴትስ እርሷን፦ ‘እኅቴ ናት’ አልህ?” ይስሐቅም፦ “በእርሷ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም አለ፦ “ይህ ያደረግህብን ምንድነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር።” አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፦ “ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት” ብሎ አዘዘ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፥ እግዚአብሔርም ባረከው። ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፥ በግና ላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፥ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጉድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፥ አፈርንም ሞሉባቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፦ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጉድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፥ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጉድጓድ አገኙ። የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፦ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተከራከሩ፥ የዚያችንም ጉድጓድ ስም “ኤሴቅ” ብሎ ጠራት፥ ለእርሷ ሲሉ ተጣልተዋልና። ሌላ ጉድጓድም ማሱ፥ ስለ እርሷም ደግሞ ተጣሉ፥ ስምዋንም “ስጥና” ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጉድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርሷም አልተጣሉም፥ ስምዋንም “ርኆቦት” ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን።” ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፥ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ እባርክሃለሁ፥ ስለ ባርያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።” በዚያም መሠዊያን ሠራ የጌታንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፥ የይስሐቅም አገልጋዮች በዚያ ጉድጓድ ማሱ።
ኦሪት ዘፍጥረት 26 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 26:2-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች