ዘፍጥረት 26:2-25
ዘፍጥረት 26:2-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “ወደ ግብፅ አትውረድ፤ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፤ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህችን ምድር ሁሉ ለአንተም፥ ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህም ለአብርሃም የማልሁለትን መሐላ ከአንተ ጋር አጸናለሁ። ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ይህችንም ምድር ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ አባትህ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፤ ትእዛዜንና ፍርዴን፥ ሥርዐቴንና ሕጌንም ጠብቆአልና።” ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ ጠየቁት፤ እርሱም፥ “እኅቴ ናት” አላቸው፤ የዚህ ስፍራ ሰዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፤ እርስዋም ውብ ነበረችና። በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጠ። የፍልስጥኤም ንጉሥ አቤሜሌክም በመስኮት ሆኖ በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከሚስቱ ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው። አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠራ፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ ሚስትህ ናት፤ እንዴትስ እርስዋን፦ ‘እኅቴ ናት’ አልህ?” ይስሐቅም፥ “በእርስዋ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው” አለው። አቤሜሌክም አለ፥ “ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? ከሕዝቡ አንዱ ባለማወቅ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፤ ኀጢአትንም ልታመጣብን ነበር።” አቤሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፥ “ይህን ሰው፥ ሚስቱንም የሚነካ ፍርዱ ክፉ ሞት ነው” ብሎ አዘዘ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ ገብስ አገኘ፤ እግዚአብሔርም ባረከው። ከፍ ከፍም አለ፤ እጅግም ታላቅ እስኪሆን ድረስ እየጨመረ ይበዛ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን፥ ብዙ በጎችንና ላሞችን፥ የእርሻ መሬትንም ገዛ፤ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጕድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፤ አፈርንም ሞሉባቸው። አቤሜሌክም ይስሐቅን፥ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፤ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፤ በጌራራም ሸለቆ ሰፈረ፤ በዚያም ተቀመጠ። ይስሐቅም የአባቱ የአብርሃም አገልጋዮች ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጕድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፤ አባቱ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበርና፤ አባቱም አብርሃም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በጌራራ ሸለቆ ውስጥ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ በዚያም ጣፋጭ የውኃ ምንጭ አገኙ። የጌራራ እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፥ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተጣሉ፤ የዚያችንም ጕድጓድ ስም “ዐዘቅተ ዐመፃ” ብሎ ጠራት፤ እነርሱ በድለውታልና። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ በዚያም ሌላ ጕድጓድ ማሰ፥ ስለ እርስዋም ደግሞ ተጣሉት፤ ስምዋንም “ጽልእ” ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ስለ እርስዋም አልተጣሉትም፤ ስምዋንም “መርኅብ” ብሎ ጠራት፤ እንዲህ ሲል፥ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፤ በምድርም አበዛን።” ከዚያም ወደ ዐዘቅተ መሐላ ሄደ። በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አባትህ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛዋለሁ።” በዚያም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፤ በዚያም ድንኳን ተከለ፤ የይስሐቅም ሎሌዎች በዚያ ጕድጓድ ማሱ።
ዘፍጥረት 26:2-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያም እግዚአብሔር ለይሥሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብጽ አትውረድ፤ ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ። ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።” ስለዚህ ይሥሐቅ በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለ ሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር። ይሥሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይሥሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይሥሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት ‘እኅቴ ናት’ ትላለህ?” አለው። ይሥሐቅም፣ “በርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው። አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ። ይሥሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም ባረከለትና በዚያ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሯቸውን የውሃ ጕድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኗቸው። አቢሜሌክም ይሥሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። ይሥሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኗቸውን የውሃ ጕድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው። የይሥሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጕድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ። የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይሥሐቅ እረኞች ጋራ ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይሥሐቅ ያን የውሃ ጕድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጕድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጕድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጕድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጕድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው። ከዚያም ይሥሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። ይሥሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ።
ዘፍጥረት 26:2-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር ተገለጠለት እንዲህም አለው፦ ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ። ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ ይባረላሉ፤ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴም ሕጌ፥ ጠብቆአልና። ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት እርሱም፦ እኅቴ ናት አለ የዚያም ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና እርስዋ ውብ ነበረችና። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኍላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌም በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ እንዲህም አለው፦ እነሆ ሚስትህ ናት እንዴትስ እርስዋን፦ እኅቴ ናትአልህ? ይስሐቅም፦ በእርስዋ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው አለው። አቢሜልውክም አለ፦ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር። አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፦ ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት ብሎ አዘዘ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ እግዚአብሔርም ባረከው። ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመተ ይበዛ ነበር፤ የበግና የላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጕድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው አፈርንም ሞሉባቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፦ ከእኛ ተለይተህ ሂድ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ በጌራራም ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸ የነበሩትን የውኃ ጕድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፤ አብርሃም ከሞተ በኍላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩን አባቱም ይጠራቸው በነብረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጕድጓድ አገኙ። የጌራራ አገር እረኞች ለይስሐቅ እረኞች ጋር፦ ውኃው የእኛ ነው ሲሉ ተከራከሩ፤ የዚይችንም ጕድጓድ ስም ኤሴቅ ብሎ ጠራት ለእርስዋ ሲሉ ተጣልተዋልና። ሌላ ጕድጓድም ማሱ ስለ እርስዋም ደግሞ ተጣሉ፤ ስምዋንም ስጥና ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ አስቋፈረ ስለ እርስዋም አልተጣሉም፤ ስምዋንም፥ ርኖቦት ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን በምድርም እንበዛለን። ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና እባርክሃለሁ ስለ ባሪያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ። በዚያም መሠዊያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ በዚይም ድንኳን ተከለ፤ የይስሐቅም ሎሌዎች በዚያ ጕድጓድ ማሱ።
ዘፍጥረት 26:2-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያም እግዚአብሔር ለይስሐቅ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፤ “ወደ ግብጽ አገር አትሂድ፤ እንድትኖርበት በምነግርህ በዚህ ምድር ተቀመጥ፤ እዚሁ ኑር፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ፤ በዚህ ዐይነት ለአባትህ ለአብርሃም የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈጽማለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ይህንንም ሁሉ ምድር አወርሳቸዋለሁ፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ። አንተን የምባርክበትም ምክንያት አባትህ አብርሃም ለእኔ ታዛዥ በመሆን የሰጠሁትን ትእዛዞች፥ ድንጋጌዎችንና ሕጎችን ሁሉ ስለ ጠበቀ ነው።” ስለዚህ ይስሐቅ መኖሪያውን በገራር አደረገ፤ የዚያ አገር ሰዎችም ስለ ርብቃ “ምንህ ናት” ብለው በጠየቁት ጊዜ “እኅቴ ናት” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ርብቃ በጣም ቈንጆ ስለ ነበረች የዚያ አገር ሰዎች በእርስዋ ሰበብ እንዳይገድሉት በመፍራት ነው። ይስሐቅ እዚያ አገር ብዙ ጊዜ ከቈየ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቤሜሌክ በመስኮት ወደ ውጪ ሲመለከት ይስሐቅና ርብቃ እንደ ባልና ሚስት በመዳራት ሲጫወቱ አየ፤ ስለዚህ አቤሜሌክ ይስሐቅን አስጠርቶ “ለካስ ርብቃ ሚስትህ ናት! ታዲያ ‘እኅቴ ናት’ ያልከው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ሚስቴ ነች ያልኩ እንደሆን ሰዎች ይገድሉኛል ብዬ ስለ ፈራሁ ነው” ብሎ መለሰ። አቤሜሌክም “ይህ በእኛ ላይ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? ከእኛ ሰዎች አንዱ በቀላሉ ሚስትህን ለመድፈር በቻለ ነበር፤ እኛንም ኃጢአተኞች ልታደርገን ነበር፤” ቀጥሎም አቤሜሌክ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የሚነካ ሰው በሞት ይቀጣል” የሚል ማስጠንቀቂያ ለሕዝቡ ሰጠ። ይስሐቅ በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ እግዚአብሔር ስለ ባረከውም በዚያኑ ዓመት መቶ እጥፍ አመረተ፤ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ስለ ሄደ እጅግ ባለጸጋ ሆነ። ብዙ የበግና የከብት መንጋ፥ እንዲሁም ብዙ አገልጋዮች ስለ ነበሩት ፍልስጥኤማውያን ቀኑበት። ስለዚህ የይስሐቅ አባት አብርሃም በሕይወት በነበረበት ዘመን የእርሱ አገልጋዮች ቆፍረዋቸው የነበሩትን የውሃ ጒድጓዶች ሁሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑአቸው። በዚያን ጊዜ አቤሜሌክ ይስሐቅን “ኀይልህ ከእኛ ይልቅ እየበረታ ስለ ሄደ፥ አገራችንን ለቀህ ውጣ” አለው። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ያንን ቦታ ለቆ በገራር ሸለቆ ውስጥ ሰፈረ፤ እዚያም ተቀመጠ። አብርሃም በሕይወት ሳለ አስቈፍሮአቸው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ግን ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች ይስሐቅ እንደገና እንዲቈፈሩ አደረገ፤ አባቱ ባወጣላቸው ስሞችም ጠራቸው። የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ የውሃ ጒድጓድ ቆፈሩና ጥሩ የምንጭ ውሃ አገኙ፤ የገራር እረኞች ግን “ይህ ውሃ የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ተጣሉ። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ጒድጓዱን “ዔሤቅ” ብሎ ሰየመው። የይስሐቅ አገልጋዮች ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ በዚህኛውም ጒድጓድ ምክንያት ሌላ ጠብ ተነሣ፤ ስለዚህ ይስሐቅ ይህን ጒድጓድ “ስጥና” ብሎ ሰየመው። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈረ፤ በዚህኛው የውሃ ጒድጓድ ምክንያት ምንም ጠብ ስላልተነሣ “እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጠን፤ በምድር ላይም እንበዛለን ሲል፥ ያንን ቦታ ‘ረሖቦት’ ” ብሎ ሰየመው። ከዚህ በኋላ ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ፤ በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍራ፤ ለአገልጋዬ ለአብርሃም በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ” አለው። ይስሐቅ በዚያ መሠዊያ ሠራና ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ መኖሪያውንም እዚያ አደረገ፤ አገልጋዮቹም ሌላ ጒድጓድ ቈፈሩ።
ዘፍጥረት 26:2-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “ወደ ግብጽ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፥ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ። ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፥ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።” ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት፥ እርሱም፦ “እኅቴ ናት” አለ፥ የዚያም ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፥ እርሷ ውብ ነበረችና። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ እንዲህም አለው፦ “እነሆ ሚስትህ ናት፥ እንዴትስ እርሷን፦ ‘እኅቴ ናት’ አልህ?” ይስሐቅም፦ “በእርሷ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም አለ፦ “ይህ ያደረግህብን ምንድነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር።” አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፦ “ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት” ብሎ አዘዘ። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፥ እግዚአብሔርም ባረከው። ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፥ በግና ላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፥ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጉድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፥ አፈርንም ሞሉባቸው። አቢሜሌክም ይስሐቅን፦ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ተቀመጠ። ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጉድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፥ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፥ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጉድጓድ አገኙ። የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፦ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተከራከሩ፥ የዚያችንም ጉድጓድ ስም “ኤሴቅ” ብሎ ጠራት፥ ለእርሷ ሲሉ ተጣልተዋልና። ሌላ ጉድጓድም ማሱ፥ ስለ እርሷም ደግሞ ተጣሉ፥ ስምዋንም “ስጥና” ብሎ ጠራት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጉድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርሷም አልተጣሉም፥ ስምዋንም “ርኆቦት” ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን።” ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት ጌታ ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፥ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፥ እባርክሃለሁ፥ ስለ ባርያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።” በዚያም መሠዊያን ሠራ የጌታንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፥ የይስሐቅም አገልጋዮች በዚያ ጉድጓድ ማሱ።