የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 26:2-25

ዘፍጥረት 26:2-25 NASV

በዚያም እግዚአብሔር ለይሥሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብጽ አትውረድ፤ ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ። ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።” ስለዚህ ይሥሐቅ በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለ ሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር። ይሥሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይሥሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይሥሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት ‘እኅቴ ናት’ ትላለህ?” አለው። ይሥሐቅም፣ “በርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው። አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ። ይሥሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም ባረከለትና በዚያ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሯቸውን የውሃ ጕድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኗቸው። አቢሜሌክም ይሥሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። ይሥሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኗቸውን የውሃ ጕድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው። የይሥሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጕድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ። የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይሥሐቅ እረኞች ጋራ ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይሥሐቅ ያን የውሃ ጕድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጕድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጕድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጕድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጕድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው። ከዚያም ይሥሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። ይሥሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}