ኦሪት ዘፍጥረት 19:15-29

ኦሪት ዘፍጥረት 19:15-29 መቅካእኤ

ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፦ “ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፥ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ” እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ራስህን አድን፥ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።” ሎጥም፥ አላቸው፦ “ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፥ እነሆ ባርያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፥ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፥ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርሷ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርሷም ትንሽ ናት፥ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርሷ ሸሽቼ ላምልጥ፥ እርሷ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?” እርሱም አለው፦ “የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፥ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፥ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ጾዓር ተባለ። ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፥ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች። አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፥ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፥ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ። እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፥ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}