ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋራ ዐብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት። ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው። እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው። ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤ እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደ ሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል። እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን ዕሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም። አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው። እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው። የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። አብርሃም በማግስቱም፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሄደ። ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቍልቍል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ። እንደዚህ አድርጎ እግዚአብሔር በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን ዐሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።
ዘፍጥረት 19 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 19:15-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች