የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ዕዝራ 9

9
የቅልቅል ጋብቻ መወገዝ
1እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው፦ “የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም እንደ ከነዓናውያን፥ ሒቲያውያን፥ ፌርዛውያን፥ ኢያቡሳውያን፥ አሞናውያን፥ ሞዓባውያን፥ ግብጻውያንና አሞራውያን ርኩሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር ሕዝቦች እራሳቸውን አልለዩም፤ 2አንዳንድ ሴቶች ልጆቻቸውን ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው ሚስት አድርገው ወስደዋል፥ ቅዱሱንም ዘር ከምድር ሕዝቦች ጋር ደባልቀዋል፤ በዚህ አለመታመን የአለቆቹና የባለሥልጣኖቹ እጅ ቀዳሚ ነበር።” 3ይህንንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና ካባዬን ቀደድሁ፥ የራሴን ጠጉርና ጢሜንም ነጨሁ፥ ደንግጬም ተቀመጥሁ። 4በእስራኤል አምላክ ቃል የሚንቀጠቀጡ ሁሉ ስለ ምርኮኞቹ አለመታመን ወደ እኔ ተሰበሰቡ፥ እኔም እስከ ሠርክ#9፥4 የሠርክ መሥዋዕት፤ የምሽት መሥዋዕት ማለት ነው። መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ።
የዕዝራ ጸሎት
5በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና ካባዬ እንደተቀደደ ከተዋረድኩበት ተነሣሁ፥ በጉልበቴም ተንበርክኬ ወደ ጌታ አምላኬ እጄን ዘረጋሁ፤ 6እንዲህም አልሁ፦ “አምላኬ ሆይ፥ አፍሬአለሁ፤ አምላኬ ሆይ፥ ፊቴንም ወደ አንተ ለማንሣት እፈራለሁ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ከፍ ብሏልና፥ በደላችንም ወደ ሰማያት ወጥቷልና። 7ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ በደል ነበርን፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናቶቻችን ለሰይፍ፥ ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተሰጠን። 8አሁንም ትሩፋን እንዲያስቀርልን፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን እንዲሰጠን፥ አምላካችንም ዓይናችንን እንዲያበራ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን እንዲሰጠን ለጥቂት ጊዜ ከጌታ ከአምላካችን ሞገስ ተሰጥቶናል። 9ባርያዎች ነን፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፥ የአምላካችንን ቤት እንድንሠራና ፍርስራሾቹን እንድንጠግን መታደስን ሊሰጠን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ግንብ#9፥9 ግንብ፤ የመከላከያ ቅጥር ሊሰጠን በፋርስ ነገሥታት ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኛ ላይ ዘረጋ። 10ስለዚህ አምላካችን ሆይ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዛትህን ትተናልና፤ 11በአገልጋዮችህ በነቢያት እንዲህ ስትል ያዘዝኸውን ‘ልትወርሱአት የምትገቡባት ምድር፥ በምድሩ ሕዝቦች ርኩሰት የረከሰች ምድር ናት፤ ከዳር እስከ ዳርም በርኩሰታቸውና በአጸያፊ ተግባራቸው ተሞልታለች። 12#ዘፀ. 34፥11-16፤ ዘዳ. 7፥1-5።ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፥ ሰላማቸውንና ደኅነንታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። ይህም እንድትበረቱ፥ የምድሩንም መልካም ነገር እንድትበሉ፥ ለልጆቻችሁ ለዘለዓለምም ውርስ እንድታወርሱ ነው።’” 13በክፉ ሥራችንና በታላቁ በደላችን ከደረሰብን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ትሩፋንን ሰጠኸን። 14ትእዛዝህን ለማፍረስ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም ሕዝቦች ጋር ለመጋባት እንመለሳለንን? አንተስ ትሩፋን የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቆጣምን? 15የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ እንደ ዛሬው እኛ አምልጠን ቀርተናል፥ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፥ በዚህ ምክንያት በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ