መጽሐፈ ዕዝራ 8
8
ከዕዝራ ጋር የተመለሱ የቤተሰብ መሪዎች
1በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች አለቆች እነዚህ ናቸው ትውልዳቸውም ይህ ነው፤ 2ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶን፥ ከኢታማር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡሽ፥ 3ከሽካንያ ልጆች፥ ከፓርዖሽ ልጆች ዘካርያስና፥ ከእርሱም ጋር መቶ ሃምሳ ወንዶች ተመዝግበው ነበር። 4ከፓሐት ሞዓብ ልጆች የዝራሕያ ልጅ ኤልይሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች፤ 5ከሽካንያ ልጆች የያሐዚኤል ልጅ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች፤ 6ከዓዲን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋር ሃምሳ ወንዶች። 7ከዔላም ልጆች የዓታልያ ልጅ ይሻዕያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች፤ 8ከሽፋጥያ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች። 9ከዮአብ ልጆች የይሒኤል ልጅ ዖባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች፤ 10ከሽሎሚት ልጆች የዮሲፍያ ልጅ፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ስድሳ ወንዶች። 11ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሀያ ስምንት ወንዶች፤ 12ከዓዝጋድ ልጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር አንድ መቶ ዐሥር ወንዶች። 13ከአዶኒቃም ልጆች የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፌሌጥ፥ ይዒኤልና ሽማዕያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች፤ 14ከቢጉቫይ ልጆች ዑታይና ዛቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች።
የቤተ መቅደስ አገልጋዮች
15ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም። 16ወደ አለቆቹም ወደ ኤሊዔዘር፥ አሪኤል፥ ሽማዕያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስ፥ ሜሹላምና እንዲሁም ወደ መምህራኑ ወደ ዮያሪብና ኤልናታን ላክሁ። 17በካሲፍያ ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ኢዶ ላክኋቸው፥ ለአምላካችን ቤት አገልጋዮችን እንዲያመጡልን በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለኢዶና ለወንድሞቹ ለቤተ መቅደስ አገልጋዮች ምን የሚነግሩአቸውን አስታወቅኳቸው። 18የአምላካችን መልካም እጅ በላያችን ላይ ስለ ነበረች፥ የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ ከሆነው ከማሕሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሼሬብያን፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን። 19እንዲሁም ሐሻብያ ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን ይሻዕያና ወንድሞቹንና ልጆቻቸው ሀያ ወንዶች። 20ዳዊትና ባለሥልጣኖቹ ሌዋውያንን እንዲያገለግሉ ከመረጧቸው የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮችን አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየሥማቸው ተጠቅሰዋል።
ጾምና ጸሎት
21በአምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንድንለምን በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። 22ንጉሡንም፦ “የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፥ ኃይሉና ቁጣውም እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው” ብለን ተናግረን ነበርና በመንገድ ካለው ጠላት እንዲያድኑን ወታደሮችና ፈረሰኞች ከንጉሡ ለመጠየቅ አፍሬ ነበር። 23ጾምን፥ አምላካችንን ስለዚህ ነገር ለመንን፤ እርሱም ልመናችንን ሰማ።
ለቤተ መቅደስ የቀረበ ስጦታ
24ከካህናቱ መሪዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሼሬብያን፥ ሐሻብያንና ከእነርሱም ጋር ዐሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤ 25ንጉሡ፥ አማካሪዎቹ፥ ባለሥልጣናቱ በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ፤ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን የብሩንና፥ የወርቁን፥ የዕቃውንም ስጦታ መዝኜ ሰጠኋቸው። 26ስድስት መቶ ሃምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፥ 27አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሀያ የወርቅ ሳሕኖች፥ ሁለት እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩ ከሚያንጸበርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠኋቸው። 28እኔም አልኋቸው፦ “እናንተ ለጌታ ተቀድሳችኋል፥ ዕቃዎቹም ቅዱስ ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለጌታ በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው፤ 29በካህናት አለቆች፥ በሌዋውያን በእስራኤል አባቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በጌታ ቤት ክፍሎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።” 30ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ለመውሰድ ብሩንና ወርቁን ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ።
ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
31በመጀመሪያው ወር በዓሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ እርሱም ከጠላት እጅና በመንገድ ላይም ከሚሸምቅ አዳነን። 32ወደ ኢየሩሳሌም ደረስን፥ በዚያም ሦስት ቀን ቆየን። 33በአራተኛውም ቀን ብሩ፥ ወርቁና ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኡሪያ ልጅ በምሬሞት እጅ ተመዘነ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ። ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባድና የቢኑይ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። 34በዚያን ሰዓት ሁሉም ነገር ተመዘነ፤ በሚዛንና በቍጥር ም ተመዘገበ።
35ከእስር የመጡት ከምርኮ የተመለሱት ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ እስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስት አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባት ጠቦቶች፥ ለኃጢአት መሥዋዕት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 36የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዝ ማዶ ላሉት ለንጉሡ እንደራሴዎችና ገዢዎች ሰጡ፥ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ