ትንቢተ ሕዝቅኤል 23:1-39

ትንቢተ ሕዝቅኤል 23:1-39 መቅካእኤ

የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንድ እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። በግብጽ አመነዘሩ፤ በወጣትነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ተዳሰሱ፥ በዚያም የድንግልናቸው የጡቶች ጫፍ ተዳበሱ። ስማቸውም፦ የታላቂቱ ኦሆላ የእኅትዋም ኦሆሊባ ነበረ። የእኔም ሆኑ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም፦ ኦሆላ ሰማርያ ናት፥ ኦሆሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት። ኦሖላም የእኔ ሆና ሳለ አመነዘረች፥ ጦረኞች ከሆኑት አሦራውያን ውሽሞችዋ ጋር በፍትወት ተከተለቻቸው። እነርሱም ሰማያዊ የለበሱ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ፈረስ የሚጋልቡ ፈረሰኞች ነበሩ። ዝሙቷንም ከተመረጡ የአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍትወት ከተከተለቻቸው ከጣዖቶቻቸው ሁሉ ጋር እራስዋን አረከሰች። ከግብጽ ጀምሮ የነበረውን አመንዝራነቷን አልተወችም፤ በወጣትነትዋ ጊዜ ወንዶች ከእርሷ ጋር ተኝተው ነበርና፥ የድንግልናዋንም የጡቶቿ ጫፎች ዳብሰው ነበርና፥ ፍትወታቸውንም አፍስሰውባት ነበርና። ስለዚህ በፍትወት በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ እጅ፥ በአሦር ልጆች እጅ አሳልፌ ሰጠኋት። እነርሱም ዕራቁትነትዋን ገለጡ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ወሰዱ፤ እርሷንም በሰይፍ ገደሉ፤ በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች፥ ፍርድም ተፈጸመባት። እኅትዋ ኦሆሊባ ይህን አየች፥ ሆኖም በፍትወቷና በአመንዝራነቷ ከእርሷ ይልቅ ብልሹ ነበረች፥ ይህም ከእኅትዋ ይልቅ የበዛ ነበር። አሦራውያንን፥ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ ጦረኞች፥ በፈረሶችን የሚጋልቡ ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶችን በፍትወት ተከተለቻቸው። እራስዋን እንዳረከሰች አየሁ፤ ሁለቱም በአንድ መንገድ ሄዱ። አመንዝራነቷን ቀጠለችበት፤ በቀይ ቀለም የተሳለ የከለዳውያን ስዕል፥ በግድግዳ ላይ የተቀረጸ የወንዶች ምስል አየች። በወገባቸው ዝናር የታጠቁ፥ በራሳቸውም ላይ መጠምጠሚያ ያንጠለጠሉ፥ ሁሉም የተወለዱባት አገር የከለዳ የሆነች የባቢሎን ልጆች የሆኑትን ባለሥልጣኖችን ይመስሉ ነበር። በዓይኗም ባየቻቸው ጊዜ በፍትወት ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። የባቢሎንም ልጆች ወደ እርሷ፥ ወደ ፍቅር አልጋ ገቡ፥ በዝሙታቸውም አረከሱአት፤ እርሷም በእነርሱ ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። ዝሙቷን ገለጠች፥ ዕርቃንዋንም ገለጠች፥ ነፍሴ ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርሷም ተለየች። ሆኖም በግብጽ ምድር ያመነዘረችበትን የወጣትነትዋን ዘመን አስባ ዝሙቷን አበዛች። ሥጋቸው እንደ አህዮች ሥጋ፥ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍትወት ተከተለቻቸው። ስለ ወጣትነት ጡቶችሽን ግብጻውያን ጡቶችሽን የዳበሱበትን ጊዜ የወጣትነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ። ስለዚህ ኦሆሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየቻቸው ወዳጆችሽን አስነሣብሻለሁ፥ እነርሱንም ከየአቅጣጫው በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። እነርሱም የባቢሎን ልጆች፥ ከለዳውያን ሁሉ ፋቁድ፥ ሾዓ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር የአሦር ልጆች ሁሉ፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ገዢዎች፥ ባለ ሥልጣናት፥ መኰንኖችና የተጠሩ፥ ሁሉም ፈረስ የሚጋልቡ ናቸው። መሣሪያ፥ ሠረገላና መንኰራኵር ይዘው፥ ብዙ ሕዝብ ሆነው በአንቺ ላይ ይመጣሉ፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቁርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፥ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። በቁጣ እንዲቀርቡሽ ቅናቴን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ፥ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቆርጣሉ፤ ቀሪሽም በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረው በእሳት ይበላል። ልብስሽን ይገፍፉሻል የሚያማምሩ ጌጣጌጦችሽን ይወስዳሉ። ሴሰኝነትሽንና ከግብጽ ምድር ያመጣሽውን ዝሙትሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፥ ዓይንሽን ወደ እነርሱ አታነሺም፥ ግብጽንም ዳግም አታስቢም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽም በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም በጥል ይቀርቡሻል፥ የድካምሽን ፍሬ ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፥ የዝሙትሽ ዕራቁትነት፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽ ይገለጣል። ከአገሮች ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን አደረጉብሽ። በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ የእርሷን ጽዋ በእጅሽ እሰጥሻለሁ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥልቅና ሰፊ የሆነውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ ብዙም ስለሚይዝ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ። የድንጋጤና የጥፋት ጽዋ በሆነው በእኅትሽ በሰማሪያ ጽዋ፥ በስካርና በኀዘን ትሞዪአለሽ። ትጠጪዋለሽ፥ ትጨልጪዋለሽም፥ ገሉን ታኝኪዋለሽ፥ ጡትሽንም ትቆራርጪአለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለረሳሽኝ፥ ወደ ኋላሽም ስለጣልሽኝ፥ አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ። ጌታ እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሆላና በኦሆሊባ ትፈርዳለህን? ርኩሰታቸውን ንገራቸው። አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፤ ከጣዖቶቻቸው ጋር አመንዝረዋል፤ ለእኔ የወለዷቸውን ልጆቻቸውን እንኳ መብል እንዲሆኑ አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፦ በዚያኑ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል፥ ሰንበቶቼንም ሽረዋል። ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ሊያረክሱት ወደ መቅደሴ ገብተዋልና፤ እነሆም በቤቴ ውስጥ ይህን አደረጉ።