ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ከአንድ እናት የተወለዱ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩ፤ ገና በወጣትነታቸው ዘማውያት በመሆን በግብጽ ሳሉ አመነዘሩ፤ በዚያችም ምድር አጐጠጐጤአቸው ተዳበሰ፤ የድንግልናቸውም ጕያ በእጅ ተሻሸ። የታላቂቱ ስም ኦሖላ፣ የእኅቷም ኦሖሊባ ነበር፤ ሁለቱም የእኔ ሆኑ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለዱ። ስማቸውም፣ ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባም ኢየሩሳሌም። “ኦሖላ የእኔ ሆና ሳለ በእኔ ላይ አመነዘረች፤ ጦረኞች ከሆኑት ጎረቤቶቿ ከአሦራውያን ውሽሞቿ ጋራ ሴሰነች፤ እነርሱም ሐምራዊ የለበሱ፣ ገዦችና አዛዦች፣ ሁሉም መልከ ቀና ጐበዛዝትና ፈጣን ፈረሰኞች ነበሩ። እርሷ በዝሙት ራሷን ምርጥ ለሆኑት አሦራውያን ሁሉ አሳልፋ ሰጠች፤ ዐብረዋት ባመነዘሩት ሰዎች ጣዖት ሁሉ ረከሰች። በግብጽ የጀመረችውን አመንዝራነቷን አልተወችም፤ በዚያ ወንዶች በወጣትነቷ ከርሷ ጋራ ተኙ፤ የድንግልናዋን ጡት አሻሹ፤ ፍትወታቸውን አፈሰሱባት። “ስለዚህ ዐብራቸው ላመነዘረች ለአሦራውያን ውሽሞቿ አሳልፌ ሰጠኋት። እነርሱም ዕርቃን አስቀሯት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቿን ነጠቋት፤ እርሷንም በሰይፍ ገደሏት፤ በሴቶችም ዘንድ መተረቻ ሆና ቀረች፤ ፍርድም ተፈጸመባት። “እኅቷ ኦሖሊባ ይህን አይታ ነበር፤ ሆኖም በፍትወቷና በዘማዊነቷ ከእኅቷ የባሰች ብልሹ ሆነች። ደግሞም ገዦችና አዛዦች፣ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ ጦረኞች፣ ፈጣን ፈረሰኞችና፣ ሁሉም መልከ ቀና ከሆኑት አሦራውያን ጐበዛዝት ጋራ አመነዘረች። ይህችም እንደ ረከሰች አየሁ፤ ሁለቱም በአንድ መንገድ ሄዱ። “በአመንዝራነቷ እየባሰች ሄደች፤ በደማቅ ቀይ ቀለም በግድግዳ ላይ የተቀረጹ የከለዳውያንን ወንዶች ምስል አየች፤ እነርሱም ወገባቸውን በቀበቶ የታጠቁና በራሳቸው ላይ ተንጠልጣይ ያለው ጥምጥም የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም የከለዳውያን ተወላጆችና የባቢሎን ሠረገላ አዛዦች ይመስሉ ነበር። ባየቻቸውም ጊዜ በፍትወት ተቃጠለች፤ ወደ ከላውዴዎን መልእክተኞች ላከችባቸው። ባቢሎናውያንም መጥተው ወደ ፍቅር መኝታዋ ገቡ፤ በፍትወታቸውም አረከሷት፤ እርሷም በእነርሱ ከረከሰች በኋላ ጠልታቸው ከእነርሱ ዘወር አለች። ግልሙትናዋን በአደባባይ በፈጸመችና ዕርቃን በገለጠች ጊዜ ከእኅቷ ዘወር እንዳልሁ፣ ጠልቻት ከርሷም ዘወር አልሁ። እርሷ ግን በግብጽ ያመነዘረችበት የወጣትነት ዘመኗ ትዝ እያላት የባሰ ዘማዊት ሆነች። በዚያም አባለዘራቸው እንደ አህያ፣ የዘር ፍሰታቸውም እንደ ድንጕላ ፈረስ ዘር ፍሰት ከሆነ ውሽሞቿ ጋራ አመነዘረች፤ በግብጽ ምድር ጕያሽን የታሸሽበትንና የወጣትነት ጡቶችሽን የተዳበስሽበትን የኰረዳነትሽን ብልግና ተመኘሽ። “ስለዚህ፣ ኦሖሊባ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጠልተሻቸው ከእነርሱ ዘወር ያልሽውን ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ አስነሣለሁ፤ እነርሱንም ከየአቅጣጫው አመጣብሻለሁ፤ እነርሱም ባቢሎናውያንና ከለዳውያን ሁሉ፣ የፋቁድ፣ የሱሔና የቆዓ ሰዎች፣ ከእነርሱም ጋራ አሦራውያን ሁሉ ናቸው። እነዚህም መልከ ቀና ጐበዛዝት ሲሆኑ፣ ሁላቸውም በፈረስ ላይ የተቀመጡ ገዦችና አዛዦች፣ የሠረገላ አዛዦችና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ነበሩ። እነርሱም የጦር መሣሪያ፣ ሠረገላና ጋሪ በመያዝ ብዙ ሕዝብ ሆነው ይመጡብሻል፤ ትላልቅና መለስተኛ ጋሻ በማንገብና የራስ ቍር በመድፋት በየአቅጣጫው ይሰለፉብሻል፤ እኔም ለፍርድ በእጃቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ በሕጋቸውም መሠረት ይቀጡሻል። የቅናት ቍጣዬን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ እነርሱም በአንቺ ላይ በቍጣ ይወጣሉ፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንቺ ወገን የተረፉትም በሰይፍ ይወድቃሉ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዱብሻል፤ የተረፉትንም እሳት ይበላቸዋል። ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽንም ይወስዱብሻል። በግብጽ የጀመርሽውን ብልግናና ሴሰኛነት ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ አንቺም ዐይንሽን ወደ እነዚህ አታነሺም፤ ከእንግዲህ ግብጽን አታስቢም። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እነሆ ተጸይፈሻቸው ከእነርሱ ዘወር ላልሽው ለጠላሻቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ። እነርሱም በጥላቻ ይቀርቡሻል፤ የለፋሽበትንም ሁሉ ይቀሙሻል፤ ከማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ያስቀሩሻል፤ የሴሰኝነትሽ ኀፍረት ይገለጣል። ብልግናሽና ገደብ የለሽ ርኩሰትሽ፣ ይህን አምጥተውብሻል፤ ከአሕዛብ ጋራ በማመንዘር በጣዖቶቻቸው ረክሰሻልና። በእኅትሽ መንገድ ስለ ሄድሽ የእርሷን ጽዋ በእጅሽ አስጨብጥሻለሁ። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰፊና ጥልቅ የሆነውን ጽዋ፣ የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ ብዙም ስለሚይዝ ስድብና ነቀፌታ ትጠግቢአለሽ። በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፣ በመፍረስና በጥፋት ጽዋ፣ በስካርና በሐዘን ትሞዪአለሽ። ትጠጪዋለሽ፤ ትጨልጪዋለሽም፤ ከዚያም ጽዋውን ትሰባብሪዋለሽ፤ ጡትሽንም ትቈራርጪአለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ረስተሽኛል፤ ወደ ኋላም ገሸሽ አድርገሽኛልና የብልግናሽንና የሴሰኝነትሽን ውጤት ትሸከሚአለሽ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? እንግዲያውስ ጸያፍ ተግባራቸውን ንገራቸው። አመንዝረዋል፤ እጃቸውም በደም ተበክሏልና። ከጣዖቶቻቸው ጋራ አመነዘሩ፤ የወለዱልኝን ልጆቻቸውን እንኳ ለእነርሱ መብል ይሆኑ ዘንድ በእሳት ሠውተውላቸዋል። ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፤ በዚያ ቀን ቤተ መቅደሴን አረከሱ፤ ሰንበታቴንም አቃለሉ። ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉባት ዕለት ወደ መቅደሴ ገብተው አረከሷት፤ እንግዲህ በቤቴ ውስጥ ያደረጉት እንዲህ ያለውን ነው።
ሕዝቅኤል 23 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 23
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 23:1-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች