ትንቢተ ሕዝቅኤል 11
11
የክፉ አማካሪዎች ፍርድ
1መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው ወደ ጌታ ቤት ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያአዛንያንንና የበናያ ልጅ ፈላጥያንን አየሁ። 2እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ክፉ ምክርን የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። 3እነርሱም፦ ቤቶች የሚሰሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት ናት፥ እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። 4ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፥ የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር።
5የጌታም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ፦ ጌታ እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔ የልባችሁን ሐሳብ አውቃለሁና። 6በዚህች ከተማ ውስጥ የገደላችኋቸውን አብዝታችኋል፥ ጎዳናዎችዋንም በተገደሉት ሞልታችኋል። 7ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ያኖራችኋቸው የተገደሉት እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ድስቱ ይህች ከተማ ናት፥ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። 8ሰይፍን ፈርታችኋል፥ እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ፥ በባዕዳንም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ላይ ፍርድ አመጣባችኋለሁ። 10በሰይፍ ትወድቃላችሁ፥ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 11ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፥ እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ። 12እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ሕጌንም አልፈጸማችሁምና፥ ነገር ግን በዙሪያችሁ እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።
13ትንቢት እየተናገርሁ ሳለሁ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፥ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ እንዲህም አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ወዮ! የእስራኤልን ትሩፍ ፈጽመህ ታጠፋለህን?
እግዚአብሔር እስራኤልን ያድሳል
14የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 15የሰው ልጅ ሆይ፥ ወንድሞችህ፥ ዘመዶችህ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ፥ “ከጌታ ራቁ፥ ምድሪቱ ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች” ብለዋል። 16ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል አርቄ ብወስዳቸውም፥ በአገሮች መካከል ብበትናቸውም፥ በሄዱባቸው አገሮች በዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ። 17ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፥ ከተበተናችሁባቸው አገሮችም እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር ለእናንተ እሰጣችኋለሁ። 18ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉን ነገር ሁሉና ርኩሱን ነገር ሁሉ ከእርሷ ያወጣሉ። 19#ሕዝ. 36፥26-28።አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ አዲስ መንፈስም በውስጣቸው አኖራለሁ፥ ከሥጋቸውም የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ 20ይህም በትእዛዜ እንዲሄዱ፥ ፍርዴንም እንዲጠብቁና እንዲፈጽሙ ነው፤ ስለዚህ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 21ልባቸው ወደ ጸያፍና ርኩስ ነገራቸው የሚከተል ግን መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22 #
ሕዝ. 43፥2-5። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። 23የጌታም ክብር ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ በምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ። 24መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ተለየ። 25ጌታ ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞቹ ተናገርሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ