የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 12

12
የይሁዳ መማረክ በስዕል ተገለፀ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2#ኢሳ. 6፥9፤10፤ ኤር. 5፥21፤ ማር. 8፥18።የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፥ እንዲያዩ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፥ እንዲሰሙም ጆሮ አላቸው ነገር ግን አይሰሙም፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። 3አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ ጓዝ ለራስህ አዘጋጅ፥ እያዩህም በቀን ወደ ምርኮ ሂድ፥ በፊታቸውም እንደ ምርኮኛ ከስፍራህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ፥ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። 4ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ እያዩህ በቀን አውጣው፥ በማታም እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። 5እያዩህም ግንቡን ቦርቡረው፥ በእርሱም አውጣው#12፥5 አሳልፈው። 6ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና እያዩህ በትከሻህ ላይ ተሸከመው፥ በጨለማም ይዘኸው ውጣ፥ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን። 7እኔም እንደታዘዝኩት አደረግሁ፥ በቀንም ጓዙን እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፥ በምሽትም ጊዜ ግንቡን በእጄ ቦረቦርሁት፥ እያዩኝም በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ በጨለማ አወጣሁት።
8በማግስቱም የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት፥ ዓመፀኛ ቤት፦ ምን እያደረግህ ነው? አላሉህምን? 10እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በውስጧ ለሚኖሩ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው። 11እንዲህም በላቸው፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፥ እኔ እንዳደረግሁት እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም ወደ ስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ። 12በመካከላቸውም ያለው ልዑል በትከሻው ላይ ተሸክሞ በጨለማ ይወጣል፥ በዚያም ሊወጡ ግንቡን ይቦረቡራሉ፥ በዓይኑም ምድሪቱን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። 13#2ነገ. 25፥7፤ ኤር. 52፥11።መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፥ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል። 14በዙሪያው ያሉ ረዳቶቹና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፥ ከኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። 15በአሕዛብ መካከል ስበትናቸው፥ በአገሮችም ስዘራቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 16በሚሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ርኩሰታቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ከእነርሱ ጥቂቶች ከሰይፍ፥ ከራብና ከቸነፈር አስቀራለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
ፍርድ ተፈፀመ እንጂ አልተላለፈም
17የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18የሰው ልጅ ሆይ፥ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፥ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በስጋት ጠጣ፤ 19ለምድሪቱም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤልም ምድር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፦ በሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ስለምትጠፋ ምግባቸውን በስጋት ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። 20ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፥ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
21የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 22የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ “ቀኖቹ ረዝመዋል፥ ራእይም ሁሉ ጠፍቶአል” የምትሉት ይህ ምሳሌ ምንድነው? 23ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቧል በላቸው። 24ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። 25ነገር ግን እኔ ጌታ የምናገረውን ቃል እናገራለሁ፥ ይፈጸማልም፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
26የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የእስራኤል ቤት እንዲህ ይላሉ፦ የሚያየው ራእይ ለብዙ ዘመን ነው፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል። 28ስለዚህም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ