ትንቢተ ሕዝቅኤል 10
10
የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መለየት
1 #
ሕዝ. 1፥26፤ ራእ. 4፥2። እኔም አየሁ፥ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ፥ ዙፋን የሚመስል ነገር ታየ። 2#ራእ. 8፥5።በፍታም የለበሰውን ሰው እንዲህ አለው፦ በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ። 3ሰውዬው ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላው። 4የጌታ ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መግቢያ ላይ ቆመ፥ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በጌታ የክብር ብርሃን ተሞላ። 5ሁሉን የሚችል አምላክ ሲናገር እንደሚያሰማው ዓይነት ድምፅ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ ተሰማ። 6በፍታ የለበሰውን ሰው ሲያዘው፦ ከኪሩቤል መካከል ከመንኰራኵሮች መካከል እሳት ውሰድ አለው፥ እርሱም ገብቶ በአንድ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ። 7ከኪሩቤል መካከል አንድ ኪሩብ እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታ በለበሰው ሰው እጅም አኖረው፥ እርሱም ይዞ ወጣ። 8ኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅ የሚመስል ታየ።
9 #
ሕዝ. 1፥15-21። እኔም አየሁ፥ እነሆ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ፥ አንድ መንኰራኵር በአንድ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ የቢረሌ ድንጋይ ይመስል ነበር። 10የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበር። 11ሲሄዱም በአራቱም ጎናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር፥ ራስ ወደዞረበት ስፍራ ወደዚያ ይከተሉ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም ነበር። 12#ራእ. 4፥8።መላ አካላቸው ሁሉ፥ ጀርባቸው፥ እጃቸው፥ ክንፋቸው፥ መንኰራኵሮቹም፥ የአራቱም መንኰራኵሮች፥ ዙሪያቸው በሙሉ በዐይኖች ተሞልተው ነበር። 13መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ “የሚሽከረከሩ መንኰራኵሮች” ተብለው ተጠሩ። 14#ሕዝ. 1፥10፤ ራእ. 4፥7።እያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፥ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛው ፊት የሰው ፊት፥ ሦስተኛው ፊት የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም ፊት የንስር ፊት ነበረ።
15ኪሩቤልም ተነሡ፥ እነዚህ በኮቦር ወንዝ ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው። 16ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፥ ኪሩቤል ከምድር ለመነሣት ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮቹም ከአጠገባቸው አይለዩም ነበር። 17የሕያዋኑ መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ስለ ነበረ እነዚህ ሲቆሙ እነዚያም ይቆሙ ነበር፥ እነዚህ ሲነሱ እነዚያም ከእነርሱ ጋር ይነሱ ነበር።
18የጌታ ክብር ከቤቱ መግቢያ ወጥቶ ከኪሩቤል በላይ ቆመ። 19ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ እኔም እያየሁ ከምድር ተነሡ፥ ሲወጡም መንኰራኵሮች በአጠገባቸው ነበሩ፥ በጌታ ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤል አምላክ ክብርም በላያቸው ላይ ነበረ።
20እነዚህ በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ናቸው፥ እኔም ኪሩቤል እንደ ነበሩ አስተዋልሁ። 21እያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ እያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ ከክንፎቻቸው ሥርም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ነበረ። 22ፊቶቻቸውም በኮበር ወንዝ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፥ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፥ እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ