መጽሐፈ መክብብ 2
2
1እኔ በልቤ እራሴን እንዲህ አልኩት፦ “ና ደስታን በማቅመስ ልፈትንህ፥ መልካምንም ቅመስ፤” ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። 2“ሳቅን፦ ዕብደት፥ ደስታንም፦ ዋጋ ቢስ” አልሁት። 3ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት አላዋቂነትንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ፤ ይህም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት የሚገባ መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስካይ ድረስ ነው። 4#1ነገ. 10፥23-27፤ 2ዜ.መ. 9፥22-27።ትልቅ ሥራን ሠራሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ገነባሁ፥ ወይንንም ተከልሁ፥ 5የአትክልት ሥፍራዎችንና ገነትን አሰናዳሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ 6በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ሠራሁ። 7#1ነገ. 4፥23።ወንዶችንና ሴቶችን ባርያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባርያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። 8#1ነገ. 10፥10፤14-22።ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችን፥ ለሰዎች ልጆች ተድላ የሚሰጡ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። 9#1ዜ.መ. 29፥25።ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸናች። 10ዐይኖቼ የፈለጉትን እንዳያዩ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። 11እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።
12እኔም ጥበብን ዕብደትንና አለማወቅን ለመመርመር ወሰንኩ፥ በፊት የተደረገውን መድገም ካልሆነ በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? 13እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከአለማወቅ እንደሚበልጥ አየሁ። 14የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ሆኖም የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደሆነ አስተዋልሁ። 15እኔም በልቤ፦ በአላዋቂ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። 16በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘለዓለም የሚሆን የጠቢብና የአላዋቂ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል! 17ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
18ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። 19ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ይሠለጥንበታል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 20እኔም ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተመልሼ ልቤን ተስፋ አስቈረጥሁት። 21ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም ጉዳት ነው። 22ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ መጨነቅ የሰው ልጅ ምን ጥቅም ያገኛል? 23#ኢዮብ 5፥7፤ 14፥1።ዘመኑ ሁሉ ስቃይ፥ ጥረትም ትካዜ ነው፥ ልቡም በሌሊት አያርፍም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
24 #
መክ. 3፥13፤ 5፥18፤ 9፥7፤ ኢሳ. 56፥12፤ ሉቃ. 12፥19፤ 1ቆሮ. 15፥32። ለሰው በመብላትና በመጠጣት፥ እንዲሁም በመጣር ከሚያገኘው ደስታ የሚሻለው ነገር የለም፥ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደተሰጠ አየሁ። 25ያለ እርሱ ፈቃድ ማን ይበላል፥ ማንስ ተድላን ይቀምሳል? 26#ኢዮብ 32፥8፤ ምሳ. 2፥6።እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፥ ለኃጢአተኛው ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ሥራን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ