በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። በመለኮቱ ኃይል በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ሰጠን። በእነዚህም አማካኝነት፥ ከክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ፥ በተስፋው ቃል ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ፥ በክብርና በበጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። በዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ ሠናይነትን ጨምሩ፥ በሠናይነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችነት መዋደድ፥ በወንድማማችነትም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ቢኖሩአችሁና ቢበዙላችሁ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ በተመለከተ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ግን የሩቁን ነገር ማየት የማይችል ዕውር ነው፤ ከቀደመው ኀጢአቱም መንጻቱን ረስቷአል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁንና መመረጣችሁን እንድታጸኑ፥ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ ይህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም። በዚህ መልክ፥ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁና፥ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ጸንታችሁ ብትኖሩም፥ ስለ እነዚህ ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። በዚህ ሕይወት እስካለሁበት ጊዜ ድረስ እናንተን ዘወትር ማነቃቃት ትክክል መስሎ ይታየኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቴ ፈጥኖ እንደሚሆን አውቃለሁና፤ ከመለየቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች፥ በየትኛውም ጊዜ ማሰብ ትችሉ ዘንድ፥ በብርቱ እተጋለሁ። ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልና መምጣቱም በነገርናችሁ ጊዜ፥ ራሳችን ግርማውን በዐይናችን አይተን የምንመሰክር እንጂ፥ በሰው ብልጠት የታቀደውን ተረት ተከትለን አይደለም። ከግርማዊው ክብር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው!” የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ገናናነትን ተቀብሏል።
2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1 ያንብቡ
ያዳምጡ 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:2-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos