2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9
9
ንግሥት ሳባ ሰሎሞንን መጎብኘትዋ
1 #
ማቴ. 12፥42፤ ሉቃ. 11፥31። የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቶና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ልትፈትነው መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ስውር ነገር አልነበረም። 3የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት በተመለከተች ጊዜ፥ 4የማዕዱንም መብል፥ የሹማምንቱንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም አለባበሳቸውንም፥ በጌታም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች። 5ንጉሡንም እንዲህ አለችው፦ “ስለ ስኬትህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 6እኔ ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኩሌታ አልነገሩኝም፤ ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ። 7በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባርያዎችህ ብፁዓን ናቸው። 8በአምላክህ በጌታ ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ሊያስቀምጥህ የወደደህ አምላክህ ጌታ ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘለዓለም ሊያጸናቸው ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድና ጽድቅ እንድታደርግ በእነርሱ ላይ አነገሠህ።”
9ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቶ የከበረም ዕንቁ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቶ ከቶ አልነበረም። 10ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም ባርያዎችና የሰሎሞን ባርያዎች የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቁ ደግሞ አመጡ። 11ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለጌታ ቤትና ለንጉሡ ቤት እርከኖችን፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና ሠራ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። 12የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የፈለገችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርሷም ተመልሳ ከባርያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች።
የሰሎሞን ታላቅ ሀብት
13በየዓመቱ ወደ ሰሎሞን የሚመጣው ወርቅ በሚዛን ሲለካ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ሲሆን፥ 14ነጋድራሶችና ነጋዴዎች የሚያመጡትን ወርቅ የሚጨምር አልነበረም፤ የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድሩም ሹማምንት ወርቅና ብር ወደ ሰሎሞን ያመጡ ነበር። 15ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 16ከጥፍጥም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አስቀመጣቸው። 17ንጉሡም ደግሞ ከዘሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በንጹሕ ወርቅም አስለበጠው። 18ከዙፋኑም ጋር ተጋጥመው ወደ ዙፋኑም የሚያስኬዱ ስድስት እርከኖችና የወርቅ ብርኩማ ዙፋኑ ነበረው፤ በዚህና በዚያም በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎችም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 19በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በማናቸውም መንግሥታት እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 20ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የነበረው ዕቃ ሁሉ ንጹሕ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር እንደ ምንም አይቈጠርም ነበር። 21ለንጉሡም ከኪራም ባርያዎች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር የዝሆንም ጥርስ ዝንጀሮና ዝጉርጉር ወፍም ይዘው ይመጡ ነበር።
22ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በሀብትና በጥበብ በለጠ። 23የምድርም ነገሥታት ሁሉ ጌታ በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ#9፥23 በሰሎሞን ዘንድ መገኘትን፤ ይመኙ ነበር። 24እያንዳንዱም ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቶውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። 25#1ነገ. 4፥26።ሰሎሞንም ለፈረሶችና ለሰረገሎች አራት ሺህ ጋጥ፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 26#ዘፍ. 15፥18፤ 1ነገ. 4፥21።ከኤፍራጥስም ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። 27ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባውንም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28#ዘዳ. 17፥16።ለሰሎሞንም ፈረሶች ከግብጽና ከየአገሩ ሁሉ ያመጡለት ነበር።
የንጉሥ ሰሎሞን መሞት
29የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ተግባራት በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ በቃላት የተጻፈ አይደለምን? 30ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ