2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 8
8
የንጉሥ ሰሎሞነን የተለያዩ ተግባራት
1እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የጌታን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 2ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ዳግመኛ ሠራቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አሰፈረባቸው።
3ሰሎሞንም ወደ ሐማት-ሱባ ሄደ አሸነፋትም። 4በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ሠራ። 5ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መቀርቀሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤት-ሖሮን ታችኛውንም ቤት-ሖሮን ሠራ። 6ባዓላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉ ከተሞች ሁሉ፥ የሠረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ለመሥራት የፈለገውን ሁሉ ሠራ።
7ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከኤዊያውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ 8የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 9ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባርያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ወታደሮች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ። 10እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሥልጣን የነበራቸው የንጉሥ ሰሎሞን ከፍተኛ ሹማምት ሁለት መቶ ኀምሳ ነበሩ።
11ሰሎሞንም፦ “የጌታ ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም” ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ ወደ ሠራላት ቤት አመጣት።
12በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በጌታ መሠዊያ ላይ ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። 13#ዘኍ. 28፥9፤10፤ ዘኍ. 28፥11-15፤ ዘፀ. 23፥14-17፤ 34፥22፤23፤ ዘኍ. 28፥16—29፥39፤ ዘዳ. 16፥16።ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው ዘወትር በየቀኑ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቁርባን ያቀርቡ ነበር።
14የጌታም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው እንዲያመሰግኑ፥ በካህናቱም ፊት እንዲያገለግሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ ጠባቂዎችንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 15እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። 16የጌታም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰበት ጊዜ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተሳካ ነበረ። የጌታም ቤት ተፈጸመ።
17ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮን-ጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ። 18ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባርያዎቹ እጅ ላከለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባርያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ኀምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ