2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10
10
ሮብዓም ላይ ዐመፅ መነሣቱ
1እስራኤልም ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ። 3ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦ 4“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ ስለዚህ አሁን አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እናገለግልሃለን።” 5እርሱም፦ “ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6ንጉሡም ሮብዓም፦ “ለዚህ ሕዝብ እንድመልስለት የምትመክሩኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7እነርሱም እንዲህ ብለው ተናገሩት፦ “ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘለዓለም ባርያዎች ይሆኑልሃል።” 8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልን’ ለሚሉኝ ሕዝብ እንድመልስላቸው የምትመክሩኝ ምንድነው?” 10ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች እንዲህ በላቸው ብለው ተናገሩት፦ “ ‘አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን’ ለሚሉህ ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ‘ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ 11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”
12ንጉሡም፦ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓብ መጡ። 13ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ፦ 14“አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። 15ጌታም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከጌታ ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16 #
2ሳሙ. 20፥1። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “በዳዊት ዘንድ ምን ድርሻ አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ! ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ! አሁን ቤትህን ተመልከት።” እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። 18ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ላከ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ላይ ዓመፀ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ