እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በጌታ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ፋሲካውንም እንዲያከብሩ የጌታ አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አከበሩ። ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳከበሩት ያለ ፋሲካ ያከበረ የለም። ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ተከበረ። ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ባሰናዳ ጊዜ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ሄደ። ኒካዑም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ውግያ የማደርገው በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ ጌታም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው ጌታ እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ።” ኢዮስያስ ግን ማንነቱን ሸሽጎ ለመዋጋት ወጣ እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በጌታም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ለመዋጋት መጣ። ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ “ክፉኛ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። አገልጋዮቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች