2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 24
24
ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ማደሱ
1ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆች ወለደ።
4ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የጌታን ቤት ለማደስ አሰበ። 5ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፥ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ።” ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። 6#ዘፀ. 30፥11-16።ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ላይ ሌዋውያን እንዲሰበስቡ ለምን አላተጋሃቸውም?” 7ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የጌታን ቤት አፍርሰዋልና፤ በጌታም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለባዓል ተጠቅመውበታልና።
8ንጉሡም አዘዘ፥ ሣጥንም ሠርተው በጌታ ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። 9የጌታም ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለጌታ እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። 10አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው ግብሩን አመጡ፥ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። 11ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምንት በመጣ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የታላቁ ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥኑ ውስጥ ያወጡ ነበር፥ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲህም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፥ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። 12ንጉሡና ዮዳሄም በጌታ ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የጌታን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የጌታንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። 13ሠራተኞችም ሠሩ፥ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የጌታንም ቤት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መለሱት፥ አጽንተውም አቆሙት። 14በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ በእርሱም ለጌታ የቤት ዕቃ፥ የአገልግሎትና የቁርባን ዕቃ፥ ሙዳዮቹም፥ የወርቅና የብርም ዕቃ ተሠራበት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር።
ኢዮአስ መክዳቱ
15ዮዳሄም ሸመገለ፥ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። 16በእስራኤልም፥ ለጌታና ለቤቱም ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። 17ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሰማቸው። 18የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ ወረደ። 19ወደ ጌታም እንዲመልሱአቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፥ እነርሱ ግን አላደመጡም።
20 #
ማቴ. 23፥35፤ ሉቃ. 11፥51። የጌታም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የጌታን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ለእናተም አሳካላችሁም፤ ጌታን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል።’ ” 21ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በጌታ ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። 22እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፦ “ጌታ ይየው፥ ይበቀለውም” አለ።
ኢዮአስ መሞቱ
23በዓመቱ መጨረሻ በኢዮአስ ላይ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፥ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። 24የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ ጌታ ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት።
25እርሱንም ትተውት በሄዱ ጊዜ በጽኑ አቊስለውት ነበር፤ የገዛ ባርያዎቹም የካህኑ የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል ሲሉ አሴሩበት፥ በአልጋውም ላይ ገደሉት፥ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26ያሴሩበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። 27የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የጌታንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ