2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21
21
ኢዮራም መንገሡ
1ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። 3አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን የበኩር ልጁ ስለ ሆነ ለኢዮራም ሰጠ። 4ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ሥልጣን ይዞ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። 5ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 6የአክአብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገው እንዲሁ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በጌታም ዘንድ ክፉ የሆነውን ነገር አደረገ። 7#1ነገ. 11፥36።ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራት ለመስጠት ስላደረገው ተስፋ፥ ጌታ የዳዊትን ቤት ለማጥፋት አልፈለገም።
ኤዶምያስ ማመፁ
8 #
ዘፍ. 27፥40። በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዓመፀ፥ ለራሱም ንጉሥ አነገሠ። 9ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ። 10ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዓመፀ፥ በዚያንም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዓመፀ፥ የአባቶቹን አምላክ ጌታን ትቶ ነበርና።
የነቢዩ ኤልያስ ደብዳቤ
11ዳግምም በይሁዳ ተራሮች ላይ በከፍታ ላይ የሚገኙ የማምለኪያ ሥፍራዎችን ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፥ ይሁዳንም አሳተው። 12ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ መጣለት፦ “የአባትህ የዳዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ 13በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ 14እነሆ፥ ጌታ ሕዝብህንና ልጆችህን ሚስቶችህንም ያለህንም ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይቀስፋል። 15አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪ ወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትያዛለህ።’ ”
16ጌታም የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን የቊጣ መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ። 17ወደ ይሁዳም ወጡ፥ ወረርዋትም፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም ሴቶች ልጆቹንም ማረኩ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አላስቀሩለትም።
ኢዮራም መታመሙና መሞቱ
18ከዚህም ሁሉ በኋላ ጌታ በማይፈወስ ደዌ አንጀቱን ቀሰፈው። 19ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፥ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበረ ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። 20መንገሥም በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጎልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናበተ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልቀበሩትም።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ