2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22

22
አካዝያስ መንገሡ
1በኢየሩሳሌም የነበሩትም ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ገድለዋቸው ነበርና። የይሁዳም ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 2አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች። 3እናቱም ክፉ እንዲያደርግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። 4የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ አባቱም ከሞተ በኋላ የአባቱ አመካሪዎች መጥፊያው እስኪሆኑ ድረስ አማከካሪዎቹ ነበሩና። 5በምክራቸውም ሄደ፥ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት። 6ከሶርያም ንጉሥ ከአዛኤል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቁስል ለመታከም ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ለማየት ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
7አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ እዲጠፋ የጌታ ፈቃድ ነበረ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር ጌታ የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ ወደ ቀባው ወደ ናሜሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ። 8ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድን ሲፈጽም የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው። 9አካዝያስንም ፈልገው፥ በሰማርያም ተሸሽጎ ሳለ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉት እንዲህም ብለው ቀበሩት፦ “በፍጹም ልብ ጌታን የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው።” ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥቱን ለመግዛት የሚችል አልነበረም።
አካዝያስ ዙፋኑን መጨበጡ
10የአካዝያስም እናት ጎቶሊያ ልጇ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን የነገሥታት ዘር ሁሉ አጠፋች። 11የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ ጎቶሊያ እንዳታስገድለው የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት እንዲሁ ሸሸገችው። 12በእነርሱም ዘንድ ተሸሽጎ በጌታ ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድሪቱ ላይ ነገሠች።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ