2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2:1-6

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2:1-6 መቅካእኤ

ሰሎሞንም ለጌታ ስም ቤተ መቅደስ፥ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥትን ለመሥራት አሰበ። ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፦ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ለመሥራት የዝግባ እንጨት እንደ ላክኽለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በጌታ ፊት መዓዛው ያማረውን ሽቶ ዕጣን ለማጠን፥ የተቀደሰውንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በጌታ በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለጌታ ስም ቤት ልሠራለትና ልቀድስለት አሰብሁ። አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ የሆነ ነው። ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ እርሱን ለመያዝ አይችልምና ለእርሱ ቤት መሥራት ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት ልሠራለት የምችል እኔ ማን ነኝ?