2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2

2
ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚደረግ ዝግጅት
1ሰሎሞንም ለጌታ ስም ቤተ መቅደስ፥ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥትን ለመሥራት አሰበ። 2ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ።
የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ጋር የተደረገ ጥምረት
3ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፦ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ለመሥራት የዝግባ እንጨት እንደ ላክኽለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። 4እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በጌታ ፊት መዓዛው ያማረውን ሽቶ ዕጣን ለማጠን፥ የተቀደሰውንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በጌታ በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለጌታ ስም ቤት ልሠራለትና ልቀድስለት አሰብሁ። 5አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ የሆነ ነው። 6#1ነገ. 8፥27፤ 2ዜ.መ. 6፥18።ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ እርሱን ለመያዝ አይችልምና ለእርሱ ቤት መሥራት ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት ልሠራለት የምችል እኔ ማን ነኝ? 7አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር አብሮ የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። 8ደግሞም ባርያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቁረጥ እንደሚያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ላክልኝ፤ እነሆ፥ ባርያዎቼ ከባርያዎችህ ጋር በመሆን 9ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኛል፥ ስለ ሆነም የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናል። 10እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባርያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”
11የጢሮስ ንጉሥም ኪራም ለሰሎሞን በላከው ደብዳቤ እንዲህ ብሎ መለስ ሰጠ፦ “ጌታ ሕዝቡን ወድዶአልና በእነርሱ ላይ አነገሠህ።” 12እንዲሁም ኪራም እንዲህ አለ፦ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለጌታም ቤተ መቅደስ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥት እንዲሠራ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ ጌታ ቡሩክ ይሁን።
13“አሁንም ኪራም-አቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ልኬልሃለሁ። 14እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ለመሥራት፥ ቅርጽም ለመሥራት ንድፍም ለመንደፍ ሌላም ነገር ሁሉ ለማድረግ እውቀት አለው፥ እርሱም ከብልሃተኛዎችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር አብሮ ይሁን። 15አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባርያዎቹ ይላክ፤ 16እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እናመጣለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”
17ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። 18ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ የሕዝቡንም ሥራ ለሚቆጣጠር የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን ሾመ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ