2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 3

3
ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መገንባቱ
1 # ዘፍ. 22፥22። ሰሎሞንም ጌታ ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የጌታን ቤት መሥራት ጀመረ። 2በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር በሁለተኛውም ቀን መሥራት ጀመረ። 3ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው መለክያ መሠረት ስልሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ። 4በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። 5ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት። 6ቤቱንም በዕንቁ አስጌጠው፤ ወርቁም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ። 7ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ።
8 # ዘፀ. 26፥33፤34። ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው። 9የምስማሮቹም ሚዛን ኀምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ።
10 # ዘፀ. 25፥18-20። በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱን ኪሩቤል ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 11የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበረ። 13የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር።
14 # ዘፀ. 26፥31። ሰሎሞንም ከሰማያዊው ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት። 15በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጉልላት አምስት ክንድ ነበረ። 16እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በዓምዶቹ ራስ ላይ አኖራቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው። 17ዓምዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፥ በቀኝም የነበረውን ስም ያኪን በግራም የነበረውን ስም ቦዔዝ ብሎ ጠራቸው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ