2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11

11
ይሁዳና ብንያም መመሸጋቸው
1ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ለመመለስ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ወታደሮች ሰበሰበ። 2የጌታም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ 4‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” የጌታንም ቃላት ሰሙ፥ ኢዮርብዓምንም ሄደው ከመውጋት ተመለሱ።
5ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። 6እርሱም ቤተ ልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን ቆረቆረ፤ 7እንዲሁም ቤት-ጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥ 8ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥ 9አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥ 10ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ፤ እነዚህም የተመሸጉ ከተሞች በይሁዳና በብንያም የሚገኙ ነበሩ። 11ምሽጎቹንም አጠነከረ፥ አዛዦችንም አኖረባቸው፥ ምግቡንም ዘይቱንም የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። 12በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ። ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ።
ካህናትና ሌዋውያን ሮብዓምን መደገፋቸው
13በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። 14የጌታም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰማሪያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 15#1ነገ. 12፥31።እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች ለአጋንንቱም ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን ሾመ። 16ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለጌታ ለመሠዋት ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፥ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ።
የንጉሥ ሮብዓም ጋብቻ
18ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች። 19እርሷም የዑስ፥ ሰማራያ፥ ዘሃም የሚባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20ከእርሷም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት። 21ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስልሳ ቁባቶች ነበሩት፥ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስልሳ ሴቶች ልጆች ወለደ። 22ሮብዓምም ንጉሥ ሊያደርገው አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23ተጠበበም፥ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በተመሸጉትም ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ስንቅ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ