1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:38-51

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:38-51 መቅካእኤ

ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎችን ሠራ፤ እያንዳንዱም ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር። ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው። ሑራም ድስቶችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ፤ በዚህ ዓይነትም ለንጉሥ ሰሎሞን ሊሠራለት የጀመረውን የጌታን ቤት ሥራ ፈጸመ፤ ከሠራቸውም ነገሮች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ሁለቱ ምሰሶዎች፥ በምሰሶዎቹም ላይ የነበሩትን ማቶቶች የሚመስሉ ጉልላቶች፥ በምሰሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑት ሁለቱ መረቦች። በእያንዳንዱ ጉልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፥ በእያንዳንዱ ጉልላት ቅርጽ ላይ በሁለት ረድፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ፥ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርጾች። ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥ ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች። ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥ ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች። ድስቶቹ፥ መጫሪያዎቹና ጐድጓዳ ሳሕኖቹ፤ ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሑራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለ ንጹሕ ነሐስ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በብረት ማቅለጫ ስፍራ ነበር። ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፥ ሰሎሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፤ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያኽል እንደሆነ ተወስኖ አልታወቀም። ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰሎሞን የሚከተሉትን ዕቃዎች አሠራ፤ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ። በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተ ደቡብ፥ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፥ አበባዎች፥ የመብራት ቀንዲሎች፥ የእሳት መቆስቆሻዎች፥ ጽዋዎች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያዎች፥ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎች፥ ማንደጃዎች፥ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችና ለቤተ መቅደሱ ውጫዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የጌታ ቤት ሁሉንም ሥራ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለጌታ ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፥ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በጌታ ቤት ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው።