1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7
7
ሰሎሞን ቤተ መንግሥቱን መሥራቱ
1ሰሎሞን ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። 2የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፥ ወርዱ አምሳ ክንድ፥ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፥ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። 3ቤቱ ከምሰ ሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፥ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፥ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። 4ትይዩ የሆኑት የሕንጻው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው። 5በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ።
6“ባለ ብዙ ምሰሶዎች” ተብሎ የተጠራው አዳራሽ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር፥ ወርዱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በብዙ ምሰሶዎች የተደገፈና ጣራ የተሠራለት መመላለሻ ታዛም ነበረው።
7ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር።
8 #
1ነገ. 3፥1። ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ ልጅ ለነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት።
9እነዚህ ሁሉ ሕንጻዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፤ ድንጋዮቹ በዚያም በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተጠርበውና ተከርክመው የመጡ ነበሩ። 10መሠረቱም የተሠራው በዚያው በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ ተዘጋጅተው በመጡ ታላላቅ ድንጋዮች ነበር፤ ከታላላቆቹም ድንጋዮች ውስጥ የአንዳንዱ ጥርብ ድንጋይ ርዝመት ሦስት ሦስት ሜትር ተኩል ሲሆን፥ የሌሎቹ ደግሞ አራት ሜትር ነበር። 11በእነዚህም ታላላቅ ድንጋዮች ላይ በልክ የተሠሩ ሌሎች ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ። 12የቤተ መንግሥቱ አደባባይ፥ የጌታ ቤት ውስጣዊ አደባባይና ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንጻ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ።
ለሑራም የተመደበለት ሥራ
13ሰሎሞንም ሑራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አስጠራ። 14ሑራም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ ቀደም ብሎ የሞተው የሑራም አባትም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሞያ ነበር፤ የሑራም እናት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፤ ሑራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ ከንጉሥ ሰሎሞን በተደረገለት ጥሪ መሠረት መጥቶ የተመደበለትን የነሐስ ሥራ ሁሉ ሠራ።
ከነሐስ የተሠሩት ሁለት ምሰሶዎች
(2ዜ.መ. 3፥15-17)
15ሑራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ስምንት ሜትር፥ የዙሪያ ስፋታቸው አምስት ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ውስጡ ክፍት የሆነ አራት ጣት ውፍረት ካለው ነሐስ ሁለት ምሰሶዎችን ሠራ። 16እንዲሁም በምሰሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የሆነ ሁለት የነሐስ ጉልላቶችን ሠራ። 17በምሰሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፤ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት፥ ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ። 18በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ። ለየአንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ።
19በመመላለሻው ምሰሶዎች አናት ላይ ያሉት ጉልላቶች ቁመታቸው አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን የአሸንድዬ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር። 20እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጉልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ።
21ሑራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምሰሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፤ ከቤተ መቅደሱ መግቢያ በር በስተ ደቡብ በኩል የቆመው ምሰሶ “ያኪን” ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሰሶ ደግሞ ቦዔዝ ተባለ። 22በምሰሶዎቹ ጫፍ ላይ የአሸንድዬ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ዓይነት ተፈጸመ።
ከነሐስ የተሠራ ገንዳ
(2ዜ.መ. 4፥2-5)
23ሑራም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ጥልቀት፥ አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የክብ ማእከል ርዝመት፤ ዐሥራ ሦስት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ። 24የገንዳው አፍ ውጫዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ፥ ቅርጾች ነበሩት። 25ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬዎች ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ፤ ኰርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ደቡብ፥ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር። 26የገንዳው ጐኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የአሸንድዬ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያኽል ውሃ የሚይዝ ነበር።
ከነሐስ የተሠሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች
27ሑራም የእያንዳንዱ ርዝመት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ወርዱ አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ ዐሥር ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ። 28የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር። 29ልሙጥ በሆነው ነገርም ላይ በአንበሶች፥ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ፤ ከአንበሶቹ፥ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርጾች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጉንጉን የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። 30እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኰራኲሮችና መንኰራኲሮቹ የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። 31የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት ዐሥራ ስምንት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርጽ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም። 32የመንኰራኲሮቹም ቁመት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር፤ መንኰራኲሮቹም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኰራኲሮችም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፤ 33መንኰራኲሮቹም የሠረገላ መንኰራኲሮችን ይመስሉ ነበር፤ ወስከምቶቻቸው፥ ቅትርቶቻቸውና ዐቃፊዎቻቸው ሁሉም ከነሐስ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። 34የእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘኖች በየግርጌአቸው ከእነርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት መደገፊያዎች ነበሩአቸው። 35በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርጽ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 36በእነዚሁ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፥ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል በተሠሩ ቅርጾች አጊጠው ነበር፤ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርጾች አጊጠው ነበር። 37እንግዲህ ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች የተሠሩት በዚህ ዓይነት ነበር። መጠናቸውና ቅርጻቸው እኩል ስለ ሆነ ሁሉም ተመሳሳይ ነበሩ።
38 #
ዘፀ. 30፥17-21። ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎችን ሠራ፤ እያንዳንዱም ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር። 39ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው።
የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች ዝርዝር ባጭሩ
(2ዜ.መ. 4፥11—5፥1)
40ሑራም ድስቶችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ፤ በዚህ ዓይነትም ለንጉሥ ሰሎሞን ሊሠራለት የጀመረውን የጌታን ቤት ሥራ ፈጸመ፤ ከሠራቸውም ነገሮች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
41ሁለቱ ምሰሶዎች፥ በምሰሶዎቹም ላይ የነበሩትን ማቶቶች የሚመስሉ ጉልላቶች፥ በምሰሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑት ሁለቱ መረቦች።
42በእያንዳንዱ ጉልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፥
በእያንዳንዱ ጉልላት ቅርጽ ላይ በሁለት ረድፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ፥ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርጾች።
43ዐሥሩ ባለ መንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥
ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች።
44ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥
ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች።
45ድስቶቹ፥ መጫሪያዎቹና ጐድጓዳ ሳሕኖቹ፤
ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሑራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለ ንጹሕ ነሐስ ነበር። 46ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በብረት ማቅለጫ ስፍራ ነበር። 47ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፥ ሰሎሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፤ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያኽል እንደሆነ ተወስኖ አልታወቀም።
48 #
ዘፀ. 30፥1-3፤ ዘፀ. 25፥23-30። ለጌታ ቤት አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰሎሞን የሚከተሉትን ዕቃዎች አሠራ፤ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ። 49#ዘፀ. 25፥31-40።በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተ ደቡብ፥ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፥ አበባዎች፥ የመብራት ቀንዲሎች፥ የእሳት መቆስቆሻዎች፥ 50ጽዋዎች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያዎች፥ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎች፥ ማንደጃዎች፥ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችና ለቤተ መቅደሱ ውጫዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ከወርቅ የተሠሩ ናቸው።
51 #
2ሳሙ. 8፥11፤ 1ዜ.መ. 18፥11። ንጉሥ ሰሎሞን የጌታ ቤት ሁሉንም ሥራ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለጌታ ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፥ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በጌታ ቤት ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ