1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 21
21
1የሶርያም ንጉሥ የአዴር ልጅ ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፥ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ንጉሦች ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፥ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም። 2ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ፦ 3የአዴር ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፥ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው” ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ። 4የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፥ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለ። 5ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው፦ የአዴር ልጅ እንዲህ ይላል፦ “ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር። 6ነገም በዚህ ጊዜ ባርያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባርያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ” አለ።
7የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፦ “ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንደሚሻ እዩ፥ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም” አለ። 8ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ፦ “አትስማው፥ እሺም አትበለው” አሉት። 9ለአዴርም ልጅ መልአክተኞች፦ “ለጌታዬ ለንጉሥ፥ ለእኔ ለባርያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፥ ይህ ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት” አላቸው፤ መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት። 10የአዴርም ልጅ፦ “ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ” ብሎ ላከበት። 11የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፦ “በቃ፥ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ” አለው። 12የአዴርም ልጅ ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባርያዎቹንም፦ “ተሰለፉ” አላቸው፥ እነርሱም በከተማይቱ ትይዩ ተሰለፉ።
13እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃለህ’ አለ።” 14አክዓብም፦ “በማን?” አለ፥ እርሱም፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በአውራጆቹ አለቆች ጉልማሶች’” አሉ፤ እርሱም፦ “ሰልፉን ማን ይጀምራል?” አለ፤ እርሱም፦ “አንተ” አለው። 15የአውራጆቹንም አለቆች ጉልማሶች ቆጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፥ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ቆጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ።
16ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፥ የአዴር ልጅ ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር። 17የአውራጆቹም አለቆች ጉልማሶች አስቀድመው ወጡ፥ የአዴርም ልጅ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም፦ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል” ብለው ነገሩት። 18እርሱም፦ “ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው” አለ። 19እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጉልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፤ ሠራዊትም ተከተላቸው። 20ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፤ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ የአዴር ልጅ በፈረሱ አመለጠ። 21የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፤ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊያ ገደላቸው።
22ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ፦ “የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ” አለው። 23#2ነገ. 9፥36።የሶርያም ንጉሥ ባርያዎች እንዲህ አሉት፦ “አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፥ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፥ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን። 24ይህንም አድርግ፥ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። 25አንተም ቀድሞ እንደጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሠረገላውንም በሠረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቁጠር፥ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን።” ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። 26በሚመጣውም ዓመት የአዴር ልጅ ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። 27የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፥ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፥ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር። 28የጌታም ሰው ቀርቦ “የእስራኤልን ንጉሥ፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሶርያውያን ጌታ የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” አለው። 29እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፤ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 21: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ