1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10
10
የንግሥተ ሳባ ጉብኝት በኢየሩሳሌም
(2ዜ.መ. 9፥1-12)
1 #
ማቴ. 12፥42፤ ሉቃ. 11፥31። ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውን ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። 2ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫኑ ሽቶ፥ የከበረ ዕንቁና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በሐሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። 3እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጉምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዓይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። 4ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች። 5በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዓይነት፥ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የደንብ ልብሳቸውንም ዓይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር። 6ንጉሥ ሰሎሞንንም እንዲህ አለችው፦ “ስለ ሥራህ ውጤትና ስለ ጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው! 7ነገር ግን እዚህ ድረስ መጥቼ በዐይኔ እስካየው ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አይሆንም፤ በእርግጥም ጥበብህና ሀብትህ በአገሬ ሳለሁ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል። 8በፊትህ ሁልጊዜ በመገኘት ጥበብ የሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ሰዎችህና ባለሟሎችህ እንዴት የታደሉ ናቸው! 9ጌታ አምላክህ ይመስገን! እርሱ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ በማድረግ በአንተ መደሰቱን ገልጦልሃል፤ ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ዘላለማዊ ስለ ሆነ ጽድቅና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎሃል።”
10ንግሥተ ሳባ ያመጣችለትን ስጦታ ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን አበረከተችለት፤ ይኸውም ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ዕንቁ ነበር፤ እርሷ ለሰሎሞን ያበረከተችው የሽቶ ብዛት ከዚያ በኋላ ከቀረበለት የሽቶ ገጸ በረከት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ነበር።
11ከኦፊር ወርቅ ያመጡለት የኪራም መርከቦች ከዚያው ከኦፊር ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቁ አምጥተውለት ነበር። 12ሰሎሞን ከዚሁ ሰንደል እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን መከታዎች፥ መዘምራን የሚያገለግሉባቸውን በገናዎችና መሰንቆዎች አሠራ፤ ይህም የሰንደል እንጨት ወደ እስራኤል አገር ከመጣው የሰንደል እንጨት ሁሉ የሚበልጥ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ይህን የመሰለ የሰንደል እንጨት ከቶ ታይቶ አያውቅም።
13ንጉሥ ሰሎሞን ከተለመደው የልግስና ስጦታው ጋር የሳባ ንግሥት የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚህ በኋላ ንግሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች።
የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
(2ዜ.መ. 9፥13-29)
14ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር። 15ይህም ሁሉ ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ ከንግድ ከሚገኘው ትርፍ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ጋር ተጨማሪ ነበር።
16ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን ጋሻ በሰባት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው። 17እንዲሁም ሦስት መቶ ታናናሽ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን በሁለት ኪሎ ያኽል ወርቅ አስለበጠው፤ እነዚህንም ሁሉ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው።
18እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው። 19ወደ ዙፋኑ መወጣጫ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ የዙፋኑ ጀርባ ራስጌው ክብ ነበር፤ በዙፋኑ ግራና ቀኝ የክንድ ማሳረፊያዎች ነበሩ፤ በክንድ ማሳረፊያዎቹ ጐን አንዳንድ የአንበሳ ምስሎች ቆመው ነበር። 20በየአንዳንዱ ደረጃ በሁለት በኩል አንዳንድ የአንበሳ ምስል በድምሩ ዐሥራ ሁለት የአንበሳ ምስሎች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በሌላ በየትኛውም አገር ተሠርቶ አይታወቅም።
21በሰሎሞን ዘመን ብር ምንም ዋጋ ስላልነበረው ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎች ሁሉና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ እንጂ ከብር አልተሠሩም፤ 22ሰሎሞን ከኪራም መርከቦች ጋር በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ ሌሎች የተርሴስ መርከቦችም ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመት ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር።
23ንጉሥ ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር። 24በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ወደ እርሱ መምጣት ይፈልጉ ነበር። 25ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር።
26 #
1ነገ. 4፥26። ሰሎሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉ ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም፥ ሌሎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ። 27#ዘዳ. 17፥17።በግዛቱም ዘመን ሁሉ በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅለው ሾላ ይቆጠር ነበር። 28#ዘዳ. 17፥16።ሰሎሞን ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ ያስመጣ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ፈረሶችን በገንዘብ ገዝተው ከቀዌ ያመጡለት ነበር። 29ሠረገሎችን ከግብጽ አገር በማስመጣት፥ ለእያንዳንዱ ሠረገላ ስድስት መቶ ጥሬ ብር፥ ለእያንዳንዱም ፈረስ አንድ መቶ ኀምሳ ጥሬ ብር ይከፍሉ ነበር፤ ከዚያም እነርሱ ለሒታውያንና ለሶርያ ነገሥታት ይሸጡላቸው ነበር።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ