የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 11

11
ሰሎሞን ከእግዚአብሔር እየራቀ መሄዱ
1 # ዘዳ. 17፥17። ሰሎሞን ብዙ የባዕዳን አገሮችን ሴቶች አፈቀረ፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ንጉሥ ልጅ ሌላ የሒታውያን፥ የሞዓባውያን፥ የዐሞናውያን፥ የኤዶማውያንና የሲዶናውያን ሴቶች ልጆችን አፈቀረ። 2#ዘፀ. 34፥16፤ ዘዳ. 7፥3፤4።ጌታ ለእስራኤላውያን፥ “አሕዛብ ሴቶችን ያገባችሁ እንደሆነ በእርግጥ ወደ አማልእክታቸው ስለሚስቡአችሁ እነርሱን አታግቡ” ብሎ አስጠንቅቆአቸው ነበር፤ እነዚህን ሰሎሞን የወደዳቸው ሴቶች ጌታ እንዳይጋቡ ከከለከላቸው ሕዝቦች መካከል ናቸው፤ ሰሎሞን ግን ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተሰባበረ። 3ሰሎሞን የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ እነርሱም ሰሎሞንን ከጌታ እንዲርቅ አደረጉት። 4በተለይም በዕድሜ እየሸመገለ በሄደ መጠን ለባዕዳን አማልክት እንዲሰግድ አደረጉት፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። 5የሲዶናውያን ሴት አምላክ ለነበረችው ለዐስታሮትና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለአጸያፊው ለዐሞናውያን አምላክ ሰገደ። 6በደል በመሥራትም ጌታን አሳዘነ፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በቅንነት በመከተል ረገድ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። 7ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ተራራ ላይ አጸያፊዎች ለሆኑት ኬሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአባውያን አምላክና ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞናውያን አምላክ የመስገጃ ስፍራዎችን አዘጋጀላቸው። 8እንዲሁም የባዕዳን አገሮች ሚስቶቹ ለየአማልክታቸው ዕጣን የሚያጥኑባቸውንና መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸውን ስፍራዎች ሠራ።
9ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ጌታ ልቡ ስለሸፈተ፥ እግዚአብሔር ተቈጣው። 10ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፥ ሰሎሞን የጌታን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ 11እንዲህም አለው፤ “ከእኔ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ሆን ብለህ ስላፈረስክና ሕጌንም ስላልፈጸምክ፥ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ ልሰጠው ወስኛለሁ። 12ይሁን እንጂ ለአባትህ ለዳዊት ስል ይህን የማደርገው አንተ ባለህበት ዘመን ሳይሆን በልጅህ መንግሥት ጊዜ ይሆናል። 13ከልጅህም ቢሆን መንግሥቱን በሙሉ አልወስድበትም፤ ለአገልጋዬ ለዳዊትና ለራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል አንድ ነገድ እተውለታለሁ።”
በሰሎሞን ላይ የተነሡበት ጠላቶች
14ስለዚህም ጌታ የኤዶም ንጉሣዊ ቤተሰብ ወገን የሆነውን ሀዳድን በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣበት። 15ዳዊት ከኤዶማውያን ጋር ይዋጋ በነበረ ጊዜ የጦር አዛዡ ኢዮአብ የሞቱትን ለመቅበር ወጥቶ የኤዶማውያንን ወንዶች ልጆች ሁሉ ፈጅቶ ነበር። 16ኢዮአብና የእስራኤል ሠራዊት የኤዶምን ወንዶች ልጆች ገድለው እስኪጨርሱ ድረስ ስድስት ወራት በዚያ ቆይተዋል። 17ከሞት የተረፉት ሀዳድና ወደ ግብጽ ሸሽተው የሄዱ ጥቂቶች ኤዶማውያን የአባቱ አገልጋዮች ብቻ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜ ሀዳድ ገና ሕፃን ነበር። 18እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ በዚያም ጥቂቶች ሰዎች ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ግብጽ ተጉዘው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም ለሀዳድ መሬትና አንድ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ ምግብ ፈቀደለት። 19ሀዳድም የንጉሡ ወዳጅ ሆነ፤ ንጉሡም የሚስቱን የጣፍኔስን እኅት ለሀዳድ ዳረለት። 20እርሷም ገኑባት ተብሎ የሚጠራውን ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርሱንም ንግሥቲቱ ወስዳ በቤተ መንግሥት አሳደገችው፤ ከንጉሡም ወንዶች ልጆች ጋር አብሮ ኖረ።
21ሀዳድ በግብጽ ሳለ የንጉሥ ዳዊትንና የሠራዊቱን አዛዥ የኢዮአብን መሞት በሰማ ጊዜ “ወደ አገሬ ተመልሼ እንድሄድ አሰናብተኝ” ሲል ንጉሡን ጠየቀ።
22ንጉሡም “ስለምን ትሄዳለህ? ወደ አገርህ ለመሄድ ያሰብከው ከቶ ምን ጎድሎብህ ነው?” አለው።
ሀዳድም “ምንም የተጓደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ ወደ ትውልድ አገሬ እንድመለስ ፍቀድልኝ” ሲል ለንጉሡ መለሰ፤
23እንደገናም ጌታ ረዞን ተብሎ የሚጠራውን የኤሊዓዳን ልጅ በሰሎሞን ላይ ጠላት አድርጎ አስነሣ፤ ረዞን የጾባ ንጉሥ ከነበረው ከጌታው ከሀዳድዔዜር ኮብልሎ፥ 24የሽፍቶች አለቃ ሆኖ ነበር፤ ይህም የሆነው ዳዊት ሀዳድዔዜርን ድል ነሥቶ የእርሱ ጦር ተባባሪዎች የሆኑትን ሶርያውያንን ከፈጀ በኋላ ነበር፤ ረዞንና ተከታዮቹም ወደ ደማስቆ ሄዱ፤ በዚያም ሲኖሩ እርሱን የሶርያ ንጉሥ እንዲሆን አደረጉት። 25ሰሎሞን በኖረበት ዘመን ሁሉ ሃዳድ ካደረሰበት ችግር በተጨማሪ ረዞን የእስራኤል ጠላት ሆነ። ስለዚህ ረዞን በሶርያ ላይ ገዢ ሆኖ በእስራኤል ላይ ጠላትነቱን ቀጠለ።
ጌታ ለኢዮርብዓም የሰጠው ተስፋ
26በሰሎሞን ላይ ያመፀው ሌላው ሰው በኤፍሬም ጸሬዳ ተብላ የምትጠራው ክፍለ ሀገር ተወላጅ የሆነ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነው፤ እርሱም ከሰሎሞን አገልጋዮች አንዱ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ ተብላ የምትጠራ ባሏ የሞተባት ሴት ነበረች። 27ኢዮርብዓም ለዐመፅ የተነሣሣበትም ታሪክ እንደሚከተለው ነው፥ በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ በመሙላት እየደለደለና የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጽሮች እየጠገነ በማደስ ላይ ነበር። 28ኢዮርብዓም ከፍ ያለ የሥራ ችሎታ ያለው ወጣት ነበር፤ ሰሎሞንም ይህ ወጣት ትጉህና ብርቱ ሠራተኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ በምናሴና በኤፍሬም ነገዶች ግዛት ውስጥ ባሉት ገባሮች ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው። 29አንድ ቀን ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በጉዞ ላይ ሳለ አዲስ መጐናጸፊያ የለበሰ፥ ከሴሎ የመጣው ነቢዩ አኪያ ከከተማ ውጪ መንገድ ላይ ብቻውን አገኘው። 30አኪያም የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ አውልቆ ከዐሥራ ሁለት ቆራረጠው። 31ኢዮርብዓምንም እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቁራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ‘መንግሥትን ከሰሎሞን ወስጄ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ 32ለአገልጋዬ ለዳዊትና ከሌላው የእስራኤል ምድር የራሴ ርስት እንድትሆን ለመረጥኳት ለኢየሩሳሌም ከተማ ስል ለሰሎሞን አንድ ነገድ አስቀርቼለታለሁ። 33ይህንንም የማደርገው ሰሎሞን እኔን ትቶ ባዕዳን የሆኑትን ዐስታሮት ተብላ የምትጠራውን የሲዶና አምላክ፥ ኬሞሽ ተብሎ የሚጠራውን የሞዓብ አምላክና ሚልኮም ተብሎ የሚጠራውን የዐሞን አምላክ ስላመለከ ነው፤ ሰሎሞን ለእኔ ታዛዥ አልሆነም፤ እርሱ አባቱ ዳዊት ለእኔ ይታዘዝ እንደ ነበር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ባለመጠበቁ በድሎአል። 34ይሁን እንጂ ከሰሎሞን መንግሥትን በሙሉ አልወስድበትም፤ በሕይወት እስካለም ድረስ በሥልጣን እንዲቆይ አደርገዋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ለመረጥኩትና ሕጎቼንና ትእዛዞቼን ለፈጸመው ለአገልጋዬ ለዳዊት ስል ነው። 35ስለዚህ መንግሥትን ከሰሎሞን ልጅ ወስጄ ለአንተ ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36ይሁን እንጂ ስሜ እንዲጠራባት በመረጥኳት በኢየሩሳሌም አገልጋዬ ዳዊት በፊቴ አንድ ዘር ይኖረው ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። 37ኢዮርብዓም ሆይ! እኔ አንተን የእስራኤል ንጉሥ አደርግሃለሁ፤ አንተ በወደድከው ግዛት ሁሉ ላይ መሪ ትሆናለህ። 38አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው በፍጹም ልብህ ብትታዘዘኝ፥ በሕጎቼና በትእዛዞቼ ጸንተህ ብትኖር፥ በእኔ ፊት ሞገስ ብታገኝ፥ እኔ ዘወትር ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥም አደርግሃለሁ፤ ለዳዊት ባደረግሁት ዓይነት ዘሮችህ ከአንተ በኋላ እንደሚነግሡ አረጋግጥልሃለሁ። 39በሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት የዳዊትን ትውልዶች እቀጣለሁ፤ ይሁን እንጂ የምቀጣቸው ለዘለዓለም አይደለም።’”
40ከዚህም የተነሣ ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ሞከረ፤ ነገር ግን ኢዮርብዓም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በመኰብለል አመለጠ፤ ሰሎሞንም እስከሞተበት ጊዜ ድረስ እዚያው ቆየ።
የሰሎሞን መሞት
(2ዜ.መ. 9፥29-31)
41ሰሎሞን ያደረገው ሌላው ነገር፥ ያከናወነው ተግባርና ጥበቡ ሁሉ በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቧል። 42ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነው። 43ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሞተ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓምም በአባቱ በሰሎሞን እግር ተተክቶ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ