1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 1
1
1ንጉሡ ዳዊትም ዕድሜው ገፍቶ ስለ ሸመገለ፥ ልብስ ደራርበው ቢያለብሱትም ሙቀት ሊሰጠው አልቻለም ነበር። 2ባርያዎቹም፦ “ንጉስ ሆይ! ከአንተ ጋር ሆና የምትንከባከብህ ወጣት ልጃገረድ ፈልገን እናምጣ፤ በጌታችንም በንጉሡ እቅፍ ተኝታ ታሞቅሃለች” አሉት። 3በሁሉም የእስራኤል ግዛት የተዋበች ቆንጆ ፈለጉ፤ አቢሻግንም ሹኔም ከምትባል ስፍራ አገኙ፤ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ። 4ልጃገረዲቱም እጅግ ውብ ነበረች። ለንጉሡም ረዳትና አገልጋይ ሆነች፤ ንጉሡ ግን ከእርሷ ጋር ግንኙነት ፈጽሞ አያውቅም ነበር።
5 #
2ሳሙ. 15፥1። ያንጊዜ የሐጊት ልጅ አዶንያስ፦ “ንጉሥ እሆናለሁ” ብሎ ተነሣሣ፤ ለራሱም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን፥ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎችን አዘጋጀ። 6አባቱም በሕይወቱ ሳለ፦ “እንዲህ ለምን ታደርጋለህ?” ብሎ ከቶ ተቆጥቶት አያውቅም ነበር። ደግሞም መልከ መልካም ነበር፤ የተወለደውም ከአቤሴሎም በኋላ ነበር። 7ስለዚህ ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር አሴረ፤ እነርሱም አዶንያስን ደገፉት። 8ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያ፥ ነቢዩም ናታን፥ ሺምዒና ሬዒ፥ የዳዊትም ተዋጊዎች ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም። 9አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዔንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይጋ ሠዋ፥ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባርያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 10ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።
11ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት፦ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የሐጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን? 12አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ። 13ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባርያህ፦ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው። 14እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ።”
15ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ እልፍኝ ገባች፥ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሹኔማይቱም አቢሻግ ታገለግለው ነበር። 16ቤርሳቤህም አጎንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፥ ንጉሡም፦ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አለ። 17እርሷም አለችው፦ “ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባርያህ፦ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ በጌታ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፥ 18አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፥ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፥ 19እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፥ ባርያህን ስሎሞንን ግን አልጠራውም። 20አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዐይን ይመለከትሃል። 21ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቆጠራለን።”
22እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ። 23ለንጉሡም፦ “እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቷል” ብለው ነገሩት፥ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ። 24ናታንም አለ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ፦ ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን? 25እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን። ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፥ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ፦ ‘አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ’ ይላሉ። 26ነገር ግን እኔን ባርያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባርያህንም ሰሎሞንን አልጠራም። 27በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባርያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?”
28ንጉሡም ዳዊት፦ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች። 29ንጉሡም፦ “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ባዳነኝ በሕያው ጌታ ቃል እገባለሁ! 30በእውነት ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በጌታ እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ” ብሎ ማለ። 31ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና፦ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘለዓለም በሕይወት ይኑር!” አለች።
32ንጉሡም ዳዊት፦ “ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ። 33ንጉሡም አላቸው፦ “የጌታችሁን ባርያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፥ 34በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቀቡት፥ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ፥ ‘ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ’ በሉ። 35በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፥ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፥ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።” 36የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፦ “ያበጅ ያድርግ፥ የጌታዬም የንጉሥ ጌታ ይህን ይናገር። 37ንጉሥ ሆይ! ጌታ ከአንተ ጋር እንደሆነ ሁሉ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ መንግሥቱንም በዘመንህ ከነበረው የበለጠ ታላቅ ያድርገው!” አለው።
38ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት። 39ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅባቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፥ ቀንደ መለከትም ነፉ፥ ሕዝቡም ሁሉ፦ “ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ!” አሉ። 40ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፥ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።
41አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፥ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ፦ “ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድነው?” አለ። 42እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፥ አዶንያስም፦ “አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ” አለ። 43ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው። 44ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ላከ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት። 45ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፥ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፥ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው። 46ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል። 47የንጉሡም ባርያዎች ገብተው፦ ‘እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ!’ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፥ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ። 48ንጉሡም ደግሞ፦ ‘ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይመስገን!’ አለ።”
49አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ። 50አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ። 51ለሰሎሞንም፦ “እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ፦ ‘ንጉሡ ሰሎሞን ባርያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ’ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል” አሉት። 52ሰሎሞንም፦ “እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጉር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፥ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደሆነ ይሞታል” አለ። 53ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፥ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም፦ “ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ