እንግዲህ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ አገልጋዮችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢራት መጋቢዎች ይቁጠረን። ከዚህም በላይ፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ያሻል። ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በማንም ሰው ዘንድ ቢፈረድብኝ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ከኅሊናዬ ምንም የለም፤ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። ስለዚህም፥ በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን የሚያወጣ ደግሞም የልብን ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ፥ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም እያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። ወንድሞች ሆይ! ስለ አንዱ በሌላው ላይ አንዳችሁም እንዳትታበዩ “ከተጻፈው አትለፍ፤” የሚለውን በእኛ እንድትማሩ፥ በዚህ ስለ እናንተ ስል ራሴንና አጵሎስን እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። አንተን እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? እንግዲህ የተቀበልክ ከሆንክ፥ እንዳልተቀበልክ የምትመካው ስለ ምንድነው? አሁንማ ሞልቶላችኋል! አሁንማ ሀብታሞች ሆናችኋል! ያለ እኛ ነግሣችኋል! እኛም ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ፥ በእርግጥ ብትነግሡ ኖሮ፥ መልካም በሆነ! እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም ትንግርት ሆነናል። እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለንም፤ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለንም፥ እንዲሁም እንንከራተታለን፤ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ክፉ ሲናገሩን በትሕትና እንመልስላቸዋለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዚህ ዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4 ያንብቡ
ያዳምጡ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos