እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን የክርስቶስ አገልጋዮች እንደ ሆንን የእግዚአብሔርንም ምሥጢር የመግለጥ ኀላፊነት የተሰጠን ባለ ዐደራዎች እንደ ሆንን አድርጎ ሊቈጥረን ይገባል። ባለ ዐደራዎችም ታማኞች ሆነው መገኘት አለባቸው። ስለ እኔ የሆነ እንደ ሆነ እናንተም ብትፈርዱብኝ ወይም ሌላ ሰው ቢፈርድብኝ ምንም ግድ የለኝም፤ በእውነቱ እኔ በራሴ ላይ እንኳ መፍረድ አልችልም። እኔ እንደማውቀው ከሆነ ኅሊናዬ አይወቅሰኝም፤ ይህም እኔ ንጹሕ መሆኔን አያስረዳም፤ ነገር ግን በእኔ ላይ የሚፈርድ ጌታ ብቻ ነው። ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ፥ ጌታ ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት በማንም ላይ አትፍረዱ፤ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በጨለማ የተሰወረውን ምሥጢር ወደ ብርሃን ያወጣዋል፤ በሰዎች ልብ የተደበቀውን ሐሳብ ይገልጠዋል፤ በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ተገቢውን ምስጋና ያገኛል። ወንድሞች ሆይ! እናንተን ለመጥቀም ብዬ በዚህ ጉዳይ እኔንና አጵሎስን እንደ ምሳሌ አድርጌ ተናገርኩ፤ ይህንንም ያደረግኹት “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ምክር ትርጒሙን ከእኛ እንድትማሩ ብዬ ነው፤ ስለዚህ በአንድ ሰው መመካት ሌላውን ሰው ግን መናቅ አይገባችሁም። አንተ ከሌሎች በምን ትበልጣለህ? ከሌላ ያልተቀበልከውስ ነገር ምን አለ? ታዲያ፥ ሁሉን ነገር የተቀበልከው ከሌላ ከሆነ እንዳልተቀበለ ሰው ስለምን ትመካለህ? አሁንማ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሁሉ አግኝታችኋል፤ አሁንማ ሀብታሞች ሆናችኋል፤ ከእኛም ተለይታችሁ ነግሣችኋል፤ በእርግጥ ብትነግሡማ ኖሮ፥ እኛም ከእናንተ ጋር አብረን ስለምንነግሥ መንገሣችሁ መልካም በሆነ ነበር፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት ተፈርዶባቸው ወደሚገደሉበት ቦታ ከሚወሰዱት ሰዎች መካከል የመጨረሻዎቹ ያደረገን ይመስለኛል፤ ከዚህም የተነሣ በዓለም ሁሉ በመላእክትም ሆነ በሰዎች ፊት እንደ ትርኢት ሆነን እንታያለን፤ እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ሆነናል፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ሆናችኋል፤ እንዲሁም እኛ ደካሞች ሆነናል፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ሆናችኋል፤ እናንተ የተከበራችሁ ሆናችኋል፤ እኛ ግን የተዋረድን ሆነናል። አሁንም ቢሆን እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደበደባለን፤ መጠለያ በማጣት እንንከራተታለን። በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ሲሰድቡንና ስማችንን ሲያጠፉ በትሕትና እንመልስላቸዋለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዚህ ዓለም ውዳቂና የምድር ጥራጊ ጒድፍ ሆነናል።
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos