1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4
4
የይሁዳ ትውልድ
1የይሁዳ ልጆች ፋሬስ፥ ኤስሮም፥ ከርሚሆር፥ ሦባል ናቸው። 2የሦባልም ልጅ ራያ ኢኤትን ወለደ፤ ኢኤትም አሑማይንና ላሃድን ወለደ። እነዚህ የጾርዓውያን ወገኖች ናቸው። 3እነዚህም የኤጣም አባት ልጆች ናቸው፤ ኢይዝራኤል፥ ይሽማ፥ ይድባሽ፥ እኅታቸውም ሃጽሌልፎኒ ትበባል ነበር። 4የጌዶርም አባት ፋኑኤል፥ የሑሻም አባት ኤጽር ነበር፤ እነዚህ የቤተልሔም አባት የኤፍራታ የበኩሩ የሆር ልጆች ናቸው። 5ለቴቁሔም አባት ለአሽሑር ሔላና ነዕራ የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። 6ነዕራም አሑዛምን፥ ኦፌርን፥ ቴምኒን፥ አሐሽታሪን ወለደችለት። እነዚህ የነዕራ ልጆች ናቸው። 7የሔላም ልጆች ዴሬት፥ ይጽሐር፥ ኤትናን ናቸው። 8ቆጽ ዓኑብን፥ ጾቤባን፥ የሃሩምንም ልጅ የአሐርሔልን ወገኖች ወለደ። 9ያቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ፤ እናቱም፦ “በጣር ወልጄዋለሁና” ብላ ስሙን፦ ያቤጽ ብላ ጠራችው። 10ያቤጽም፦ “እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ይሁን፤ እንዳይጎዳኝም ከክፋት ጠብቀኝ” ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው።
11የሹሐም ወንድም ክሉብ የኤሽቶንን አባት ምሒርን ወለደ። 12ኤሽቶንም ቤትራ-ፋንና ፋሴሐን የዒርናሐሽንም አባት ተሒናን ወለደ፤ እነዚህ የሬካ ሰዎች ናቸው። 13የቄኔዝም ልጆች ጎቶንያልና ሠራያ ነበሩ። የጎቶንያልም ልጅ ሐታት ነበረ። 14መዖኖታይ ዖፍራን ወለደ። ሠራያም የጌ-ሃራሽምን አባት ኢዮአብን ወለደ፤ እነርሱም ጠራቢዎች ነበሩ። 15የዮፎኒም ልጅ ካሌብ ልጆች ዒሩ፥ ኤላ፥ ነዓም ነበሩ፤ የኤላም ልጅ ቄኔዝ ነበረ። 16የይሃሌልኤል ልጆች ዚፍ፥ ዚፋ፥ ቲርያ፥ አሣርኤል ነበሩ። 17የዕዝራም ልጆች ዬቴር፥ ሜሬድ፥ ዔፌር፥ ያሎን ነበሩ፤ የሜሬድም ሚስት ማርያምን፥ ሸማይን፥ የኤሽትምዓን አባት ይሽባን ወለደች። 18አይሁዳዊቱም ሚስቱ የጌዶርን አባት ዬሬድን፥ የሦኮንም አባት ሔቤርን፥ የዛኖዋንም አባት ይቁቲኤልን ወለደች። እነዚህም ሜሬድ ያገባት የፈርዖን ልጅ የቢትያ ልጆች ናቸው። 19የሆዲያ ሚስት የነሐም እኅት ልጆች የገርሚው የቅዒላ አባትና ማዕካታዊው ኤሽትሞዓ ነበሩ። 20የሺሞንም ልጆች አምኖን፥ ሪና፥ ቤን-ሐናን፥ ቲሎን ነበሩ። የይሽዒም ልጆች ዞሔትና ቢን-ዞሔት ነበሩ። 21የይሁዳም ልጅ የሴሎም ልጆች የሌካ አባት ዔር፥ የመሪሳ አባት ለዓዳ፥ ከአሽቤዓ-ቤት የሚሆኑ ጥሩ በፍታ የሚሠሩ ወገኖች፥ 22ዮቂም፥ የኮዜባ ሰዎች፥ ኢዮአስ፥ ሞዓብን የገዛ ሣራፍ፥ ያሹቢሌሔም ነበሩ። ይህ መዝገብ ጥንታዊ ነው። 23እነዚህ በነጣዒምና በጋዴራ የሚቀመጡ ሸክላ ሠራተኞች ነበሩ። በዚያ የንጉሡን ሥራ ለመሥራት በእርሱ ዘንድ ይቀመጡ ነበር።
የስምዖን ትውልድ
24የስምዖንም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ያሚን፥ ያሪን፥ ዛራ፥ ሳኡል ነበሩ፤ 25እንዲሁም ልጁ ሰሎም፥ ልጁ ሚብሣም፥ ልጁ ሚሽማዕ ነበሩ። 26የሚሽማዕም ልጆች፤ ልጁ ሃሙኤል፥ ልጁ ዘኩር፥ ልጁ ሰሜኢ ነበሩ። 27ለሰሜኢም ዐሥራ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ለወንድሞቹ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፥ ወገናቸውም ሁሉ እንደ ይሁዳ ልጆች አልተባዙም። 28#ኢያ. 19፥2-8።እነርሱ የሰፈሩት በቤር-ሳቤህ፥ በሞላዳ፥ በሐጸርሹዓል፥ 29በቢልሃ፥ በዔጼም፥ በቶላድ፥ 30በቤቱኤል፥ በሔርማ፥ በጺቅላግ፥ 31በቤት-ማርካቦት፥ በሐጸር-ሱሲም፥ በቤት-ቢሪ፥ በሸዓራይም ነበር። እስከ ዳዊትም መንግሥት ድረስ ከተሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። 32መንደሮቻቸው ኤጣም፥ ዐይን፥ ሬሞን፥ ቶኬን፥ ዓሻን፥ አምስቱ ከተሞች ነበሩ፤ 33እስከ በኣልም ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበሩ መንደሮቻቸው ሁሉ ነበሩ። መቀመጫቸውና የትውልዳቸው መዝገቦች እነዚህ ናቸው። 34ምሾባብ፥ የምሌክ፥ የአሜስያስ ልጅ ኢዮስያ፥ 35ኢዮኤል፥ የዮሺብያ ልጅ፥ የሠራያ ልጅ የዓሢኤል ልጅ ኢዩ፥ 36ኤልዮዔናይ፥ ያዕቆባ፥ የሾሐያ፥ ዓሣያ፥ ዓዲዔል፥ ዩሲምኤል፥ በናያስ፥ 37የሺፊ ልጅ ዚዛ፥ የአሎን ልጅ የይዳያ ልጅ የሺምሪ ልጅ የሸማያ ልጅ፤ 38እነዚህ በስማቸው የተጠሩ በወገኖቻቸው ላይ አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች እጅግ በዝተው ነበር። 39ለመንጎቻቸው መሰማሪያ ለመፈለግ ወደ ጌዶር መግቢያ እስከ ሸለቆው ምሥራቅ ድረስ ሄዱ። 40የለመለመም እጅግም ያማረ መሰማሪያ አገኙ፥ ምድሪቱም ሰፊ ጸጥታም ያለላትና ሰላም የሰፈነባት ነበረች፤ በቀድሞም ጊዜ በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ከካም ወገን ነበሩ። 41እነዚህም በስማቸው የተጻፉ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን መጥተው ድንኳኖቻቸውንና በዚያ የተገኙትን ምዑናውያንን መቱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ፈጽመው አጠፉአቸው፤ በዚያም ለመንጎቻቸው መሰማሪያ ነበረና በስፍራቸው ተቀመጡ። 42የስምዖንም ልጆች አምስት መቶ ሰዎች ወደ ሴይር ተራራ ሄዱ፤ አለቆቻቸውም የይሽዒ ልጆች፥ ፈላጥያ፥ ነዓርያ፥ ረፋያ፥ ዑዝኤል ነበሩ። 43ያመለጡትንም የአማሌቃውያንን ትሩፋን መቱ፥ በዚያም እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጠዋል።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ