1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5

5
የሮቤል ትውልድ
1 # ዘፍ. 35፥22፤ 49፥3፤4። የእስራኤልም በኩር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኩር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኩርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኩርናው ጋር አልተቈጠረም። 2#ዘፍ. 49፥8-10።ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኩርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ። 3የእስራኤል በኩር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ። 4#2ነገ. 15፥29።የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥ ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ 5ልጁ ሚካ፥ ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ 6የአሦር ንጉሥ ቴልጌል-ቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱም የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ። 7ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥ ዘካርያስ፥ 8እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ ነበር፤ 9በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ። 10በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ።
የጋድ ትውልድ
11የጋድም ልጆች ከሮቤል ነገድ አጠገብ ባለው በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ ተቀመጡ። 12አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በባሳን ተቀመጡ። 13የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ እነርሱም ሰባት ነበሩ። 14እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ። 15የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ አኪ ነበረ። 16በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰማሪያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር። 17እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ።
18የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ የውግያ ስልት የሚያውቁ ተዋጊዎችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ። 19ከአጋራውያንና ከይጡር ከናፊሽና ከናዳብ ጋር ተዋጉ። 20በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ እነርሱንም ረዳቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተላልፈው ተሰጡ። 21ከእንስሶቻቸውም ኀምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ። 22ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ።
የምናሴ የነገድ እኩሌታ
23የምናሴ የነገድ እኩሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣል-አርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ። 24የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ።
25የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ። 26#2ነገ. 15፥19፤ 2ነገ. 15፥29፤ 2ነገ. 17፥6።የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌል-ቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ አቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ