የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23

23
የሌዋውያን ወገኖችና አገልግሎታቸው
1 # 1ነገ. 1፥1-40። ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2የእስራኤልንም ሹማምንት ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። 3ሌዋውያንም ዕድሜአቸው ሠላሳ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑት ተቈጠሩ፤ በእያንዳንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ተቈጠሩ፤ ድምራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበር። 4ከእነዚህም ውስጥ የጌታን ቤት ሥራ የሚሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ። ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ። 5አራቱ ሺህም የደጁ ጠባቂዎች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሰሩት በዜማ ዕቃዎች ጌታን ያመሰግኑ ነበር።
6ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 7ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። 8የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ። 9የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። 11አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
12የቀነዓት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። 13#ዘፀ. 28፥1።የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ እንዲሆን ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘለዓለም በጌታ ፊት እንዲያጥኑና እንዲያገለግሉ፥ በስሙም ለዘለዓለም እንዲባርኩ ተለይተው ነበር። 14የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። 16የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። 17የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። 18የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። 19የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማሪያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ። 20የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።
21የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። 23የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።
24የጌታን ቤት አገልግሎት በሠሩ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። 25ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘለዓለም ይቀመጣል። 26#ዘዳ. 10፥8።ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም።” 27በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመትና ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። 28#ዘኍ. 3፥5-9።“ሥራቸውም የጌታን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ በሚሰጡተት አገልግሎት አሮንን ልጆች መርዳት፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት መሥራት ነበረ። 29ደግሞም የተቀደሰ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቁርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በመለክያ ሁሉ ያገልግሉ ነበር። 30እንዲሁም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው ጌታን በማመስገንና በማክበር፥ 31በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በጌታ ፊት ዘወትር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ፥ 32ለጌታም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት በመጠበቅ ያገለግሉ ነበረ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ