1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22
22
1ዳዊትም፦ “ይህ የጌታ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል የሚቃጠለው መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ ነው” አለ።
ንጉሥ ዳዊት መቅደሱን ለመሥራት መዘጋጀቱ
2ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች እንዲሰበስቡ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች እንዲወቅሩ ጠራቢዎችን አኖረ። 3ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። 4ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር የሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። 5ዳዊትም እንዲህ ብሏልና፦ “ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለጌታም የሚሠራው ቤት በአገሩ ሁሉ በስሙና በክብሩ እጅግ ታላቅና ዝነኛ ሊሆን ይገባል፤ እኔም ስለዚህ ዝግጅትን አደርጋለሁ።” ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ የግንባታ ቁሳቁስ አዘጋጀ።
ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንንና ሹማምንቱን ማዘዙ
6ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ስም ቤት እንዲሠራ አዘዘው። 7#2ሳሙ. 7፥1-16፤ 1ዜ.መ. 17፥1-14።ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ፦ “ልጄ ሆይ! እኔ ለአምላኬ ለጌታ ቤት እንድሠራ በልቤ አስቤ ነበር። 8ነገር ግን የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ ‘እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ውግያ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። 9እነሆ፥ ልጅ ይወለድልሃል፤ እርሱም ሰላም ያለው ሰው ይሆናል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። 10እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ።’ 11አሁንም፥ ልጄ ሆይ! ጌታ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የጌታን ቤት ሥራ። 12ብቻ የአምላክህን የጌታን ሕግ እንድትጠብቅ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሰልጥንህ። 13#ኢያ. 1፥6-9።ጌታ ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ለመፈጸም ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ። 14አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለጌታ ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ በሚዛንም የማይመዘን ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም በዚያ ላይ ጨምርበት። 15በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይ ወቃሪዎችና እንጨት ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉህ። 16የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ ጌታም ከአንተ ጋር ይሁን።”
17ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን እንዲያግዙት የእስራኤልን ሹማምንት ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 18“አምላካችሁ ጌታ ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በጌታና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። 19አሁንም አምላካችሁን ጌታን ለመሻት ልባችሁንና ነፍሳችሁን ለእርሱ አሳልፋችሁ ስጡ፤ ለጌታም ስም ወደሚሠራው ቤት የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ለማምጣት ተነሥታችሁ የጌታን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ