የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሶፎንያስ 3

3
የኢየሩሳሌም በደልና ወደ ፊት የምታገኘው ቤዛነት
1በኃጢአት ሕዝብዋን በመጨቈን ለረከሰች፥ ዐመፀኛ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! 2ማንንም አታዳምጥም፤ ተግሣጽም አትቀበልም፤ በእግዚአብሔር አትተማመንም፤ ወደ አምላክዋም አትቀርብም። 3መሪዎችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ዳኞችዋም ለነገ ሳያስተርፉ ያገኙትን ሁሉ በልተው እንደሚጨርሱ እንደ ተራቡ የማታ ተኲላዎች ናቸው። 4ነቢያትዋ በትዕቢት የተወጠሩና በተንኰል የተሞሉ ናቸው፤ ካህናትዋ የተቀደሰውን ያረክሳሉ፤ በሕግም ላይ ያምፃሉ። 5ጻድቁ እግዚአብሔር በርስዋ ውስጥ አለ፤ እርሱ ስሕተት አያደርግም፤ እርሱ በየቀኑ ፍርድን ይሰጣል፤ በየማለዳው ይህን ከማድረግ አይቈጠብም፤ ክፉ አድራጊ ሕዝብ ግን ኀፍረት የለውም።
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብ “መንግሥታትን አጠፋሁ፤ ምሽጎቻቸውን አፈራረስኩ፤ መንገዶቻቸውን ማንም የማይተላለፍባቸው ባዶ አድርጌአቸዋለሁ፤ ከተሞቻቸውን ሕዝብ የሌለባቸው፥ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ አድርጌአቸዋለሁ። 7እኔም ይህን ሁሉ በማድረጌ ‘ሕዝቤ ያከብረኛል፤ ተግሣጼንም ይቀበላል፤ የደረሰበትንም ተግሣጽ ሁሉ አይረሳም’ ብዬ ነበር፤ ሕዝቤ ግን እየባሰበት ሄደ፤ በክፉ ሥራውም ረከሰ።”
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ጥቂት ታገሡ፤ በእነርሱ ላይ የምፈርድበት ጊዜ ይመጣል፤ ሕዝቦችንና መንግሥታትን ሰብስቤ ኀይለኛ ቊጣዬን አወርድባቸዋለሁ፤ ከቊጣዬም ኀይለኛነት የተነሣ መላዋ ምድር ትጠፋለች።
9“በዚያን ጊዜ ሕዝቦች ንጹሕ ንግግር እንዲናገሩ አደርጋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ሁሉም የእኔን የእግዚአብሔርን ስም እንዲጠሩና በአንድነት እንዲያገለግሉኝ ነው። 10በስደት ተበታትነው የሚኖሩት ወገኖቼ ያመልኩኝ ዘንድ ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ መባ ይዘውልኝ ይመጣሉ። 11ትዕቢተኞችንና ትምክሕተኞችን ከመካከላችሁ ስለማስወግድ በእኔ ላይ ስለ ፈጸማችሁት በደል በዚያን ጊዜ አታፍሩበትም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ አትታበዩም። 12ከመካከላችሁ ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ ትሑታን ሰዎችን አስቀራለሁ፤ እነርሱም በእኔ የሚታመኑና የእኔንም ርዳታ የሚሹ ይሆናሉ። 13ከምርኮ የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ በማንም ላይ ክፉ ነገር አያደርጉም፤ ሐሰት አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም አያታልሉም፤ ስለዚህም ተመግበው በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።” #ራዕ. 14፥5።
የደስታ መዝሙር
14የጽዮን ልጅ ሆይ! ዘምሪ!
የእስራኤል ሕዝብ ሆይ!
ዘምሩ! እልልም በሉ!
የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሆይ!
በሙሉ ልባችሁ ደስ ይበላችሁ!
ሐሴትም አድርጉ።
15እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ያስተላለፈውን
የቅጣት ፍርድ አንሥቶላችኋል፤
ጠላቶቻችሁንም አስወግዶላችኋል፤
የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው፤
ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት ይደርስብናል ብላችሁ አትፈሩም።
16በዚያን ጊዜ ስለ ኢየሩሳሌም እንደዚህ ይባልላታል፤
“የጽዮን ከተማ ሆይ! አትፍሪ!
ክንዶችሽም አይዛሉ!
17እግዚአብሔር አምላክሽ ከአንቺ ጋር ነው፤
በኀይሉም ድልን ያጐናጽፍሻል፤
እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤
በፍቅሩም ያድስሻል፤
ሕዝቦች በበዓል ቀን በመዝሙር እንደሚያደርጉት፥
እርሱ በአንቺ ይደሰታል።”
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥
“በበዓል ቀን እንደሚደረገው የደስታ ስሜት እንዲሰማሽ አደርጋለሁ፤
ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ኀፍረት አይደርስብሽም።
19የሚያስጨንቁሽን ሁሉ በዚያን ጊዜ እቀጣለሁ፤
ያነከሱትን ሁሉ አድናለሁ፤
የተገለሉትን መልሼ እሰበስባቸዋለሁ፤
ኀፍረት እንዲሰማቸው ተደርገው በነበሩበት ቦታ ሁሉ
ኀፍረታቸውን ወደ ምስጋናና ክብር እለውጣለሁ።”
20እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“በዚያን ጊዜ ሰብስቤ ወደ ሀገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤
ንብረታችሁን ሁሉ ዐይናችሁ እያየ በምመልስላችሁ ጊዜ
በምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት
ዝነኞችና የተመሰገናችሁ ትሆናላችሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ