የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሶፎንያስ 2

2
የንስሓ ጥሪ
1እናንተ የማታፍሩ ሕዝቦች በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ 2አለበለዚያ ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ትሆናላችሁ፤ እንደ እሳት የሚነደው የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣባችኋል፤ ኀይለኛው የእግዚአብሔር የቊጣ ቀን ይመጣባችኋል። 3ትእዛዞቹን የምትፈጽሙ፥ በምድሪቱ የምትኖሩ፥ እናንተ ትሑታን ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ የጽድቅን ሥራ ሥሩ፤ በትሕትናም ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ቊጣውን በሚገልጥበት ቀን ምናልባት ከቅጣት ታመልጡ ይሆናል።
በሌሎች ሕዝቦች ላይ የተላለፈ ፍርድ
4ጋዛ ተለቃ ሰው የማይኖርባት ትሆናለች፤ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ የአሽዶድ ነዋሪዎች በቀትር ከመኖሪያቸው ይባረራሉ፤ የዓቃሮንም ሰዎች ከከተማይቱ ተፈናቅለው ይወጣሉ። 5እናንተ በባሕር ዳር የምትኖሩ ከሪታውያን ማለት ፍልስጥኤማውያን ወዮላችሁ! የእግዚአብሔር ፍርድ በእናንተ ላይ ደርሷል፤ የፍልስጥኤም ምድር ለሆንሽው ከነዓን ወዮልሽ አንድ እንኳ ነዋሪ እንዳይኖርብሽ አድርጌ አጠፋሻለሁ። 6በባሕር ዳር ያለው ምድራችሁ የከብት ማሰማሪያ፥ የእረኞች መኖሪያና የመንጋዎች ማደሪያ በረት ይሆናል። 7እግዚአብሔር አምላካቸው ስለሚንከባከባቸውና ንብረታቸውን ስለሚመልስላቸው ከብቶቻቸውን ያሰማሩበት ዘንድ የባሕሩ ዳር ከይሁዳ ሕዝብ ለተረፉት ርስት ይሆናል፤ በየምሽቱም በአስቀሎና ቤቶች ያድራሉ።
8የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ ላይ የደረሰውን የሞአብን ሕዝብ ፌዝና የአሞንን ሕዝብ ስድብ ሰምቼአለሁ፤ እነርሱም እንዴት አድርገው እንዳፌዙባቸውና ርስታቸውንም ለመውሰድ እንደ ዛቱባቸው ዐውቄአለሁ። #ኢሳ. 15፥1—16፥14፤ 25፥10-12፤ ኤር. 48፥1—49፥6፤ ሕዝ. 21፥28-32፤ 25፥1-11፤ አሞጽ 1፥13-15። 9እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ፥ ሞአብ እንደ ሰዶም አሞንም እንደ ገሞራ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም በዳዋና በጨው ጒድጓድ ተወራ ለዘለቄታ ባድማ ትሆናለች፤ ከሞት የተረፈው ሕዝቤ ይበዘብዛቸዋል ንብረታቸውንም ይወርሳል።” #ዘፍ. 19፥24።
10የሞአብና የዐሞን ሕዝብ በሠራዊት አምላክ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስላፌዙና ስለ ዛቱ ይህ ቅጣት የሚደርስባቸው ለትዕቢታቸው አጸፋ የሚከፈል ዕድል ፈንታቸው ስለ ሆነ ነው። 11በምድራቸው ያሉትን ሐሰተኞች አማልክት ሁሉ በማጥፋቱ እግዚአብሔር በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤ በባሕር ጠረፍና በደሴቶች የሚኖሩ መንግሥታት ሁሉ በያሉበት ለእርሱ ይሰግዳሉ።
12እናንተም ኢትዮጵያውያን በሰይፌ ትገደላላችሁ። #ኢሳ. 18፥1-7።
13እግዚአብሔር በኀይሉ በሰሜን የምትገኘውን አሦርን ያጠፋል፤ የነነዌን ከተማ ባድማ ያደርጋታል፤ እንደ ምድረ በዳም ያደርቃታል። 14የአራዊት መንጋዎች በእርስዋ ይኖራሉ፤ ልዩ ልዩ ዐይነት ጒጒቶች በጒልላትዋ ላይ ይኖራሉ፤ በየመስኮቱም ይጮኻሉ፤ በሊባኖስ ዛፍ የተሠራው ወለል ስለሚላቀቅ በመድረኩ ላይ ጥፋት ይደርሳል። 15“ከእኔ በቀር ሌላ የለም” ብላ በመዝናናትና ራስዋን በማስደሰት ትኖር የነበረችው ከተማ እንዴት የአራዊት መመሰጊያ ባድማ ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ በእጁ እየጠቈመ ያፏጭባታል። #ኢሳ. 10፥5-34፤ 14፥24-27፤ ናሆም 1፥1—3፥19።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ