ትንቢተ ዘካርያስ 3
3
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ ሊቀ ካህናቱ ያየው ራእይ
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ በራእይ አሳየኝ፤ ሰይጣንም ኢያሱን ለመክሰስ በስተቀኙ ቆሞ ነበር። #ዕዝ. 5፥2፤ ራዕ. 12፥10። 2የእግዚአብሔርም መልአክ ሰይጣንን “አንተ ሰይጣን! እግዚአብሔር ይገሥጽህ! ኢየሩሳሌምን የሚወድ እግዚአብሔር ይገሥጽህ! ይህ ሰው እኮ ከእሳት ውስጥ ተርፎ እንደ ወጣ እንጨት ነው” አለው። #ይሁዳ 9።
3ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። 4መልአኩም በፊቱ ቆመው የሚያገለግሉትን “ይህን ያደፈ ልብስ አውልቁለት!” ብሎ አዘዛቸው፤ ወደ ኢያሱም መለስ ብሎ “እነሆ በደልህን አስወግጄልሃለሁ፤ አዲስ የክብር ልብስም አለብስሃለሁ” አለው።
5መልአኩም አገልጋዮቹን “ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉለት!” ብሎ አዘዘ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ የእግዚአብሔር መልአክ እዚያው ቆሞ እንዳለ አገልጋዮቹ ኢያሱን አዲስ ልብስ አለበሱት።
6ከዚህ በኋላ መልአኩ ኢያሱን በማስጠንቀቅ፦ 7የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል አለው፦ “አካሄድህ እንደኔ ፈቃድ ቢሆን፥ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብታደርግ፥ በቤተ መቅደሴ የአስተዳዳሪነትን፥ በአደባባዮቼም የበላይነትን ሥልጣን እሰጥሃለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መላእክት ጋር በእኔ ፊት መግባትና መውጣት እንድትችል ባለሟልነትን እሰጥሃለሁ። 8ሊቀ ካህናት ኢያሱ ሆይ! ይህን ስማ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር በክህነት የምታገለግሉና ወደ ፊት ለሚሆነው መልካም ነገር ምልክት የምትሆኑ ይህን አድምጡ፤ ‘ቅርንጫፍ’ ተብሎ የሚጠራውን አገልጋዬን ወደ ፊት እልካለሁ። #ኤር. 23፥5፤ 33፥15፤ ዘካ. 6፥12። 9እነሆ፥ በኢያሱ ፊት ሰባት ቅርጽ ያለው አንድ ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም ላይ የጽሑፍ መግለጫ እቀርጻለሁ፤ የዚህችንም አገር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ። 10ያም ቀን ሲደርስ ከእናንተ እያንዳንዱ በወይኑና በበለሱ ተክል ሥር ጐረቤቱን ግብዣ እየጠራ ተድላ ደስታ ያደርጋል።” #ሚክ. 4፥4።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997