ትንቢተ ዘካርያስ 4
4
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ መቅረዝ ያየው ራእይ
1ያነጋግረኝ የነበረው መልአክ እንደገና መጥቶ ከእንቅልፉ እንደሚቀሰቀስ ሰው ቀሰቀሰኝ፤ 2“ይህ የምታየው ምንድን ነው?” ብሎም ጠየቀኝ።
እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩለት፦ “ሰባት መብራቶች ያሉበት አንድ የወርቅ መቅረዝ አያለሁ፤ በአናቱም ላይ የዘይት ማሰሮ አለ፤ ሰባቱም መብራቶች የክር ማስተላለፊያ ቧንቧ አላቸው። 3በመቅረዙም አጠገብ ሁለት የወይራ ዛፎች በማሰሮው ግራና ቀኝ ይታያሉ፤” #ራዕ. 11፥4። 4እኔም ያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “ጌታዬ ሆይ! እነዚህ የምን ምሳሌዎች ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።
5እርሱም “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ። እኔም “ጌታዬ ሆይ! አላውቅም” አልኩት። 6ለዘሩባቤል እንዳስታወቀው መልአኩ የነገረኝ የሠራዊት አምላክ ቃል ይህ ነው፤ “ድል የምትነሣው በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም። #ዕዝ. 5፥2። 7እንደ ተራራ በፊትህ የተደቀነው መሰናክል ሁሉ ይወገዳል፤ ቤተ መቅደሱንም መልሰህ ትሠራለህ፤ የመደምደሚያውንም ድንጋይ በስፍራው መልሰህ በምታኖርበት ጊዜ ሕዝቡ ‘እንዴት ውብ ነው! ውብ ነው!’ እያሉ የደስታ ድምፅ ያሰማሉ።”
8እንደገናም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 9“የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤተ መቅደስ መሠረት ጥለዋል፤ እጆቹም ይፈጽሙታል፤ ያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እኔን ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። 10ትንሽ ነገር የሚደረግበትን ቀን የናቀ ቱምቢውን በዘሩባቤል እጅ ሲያይ ይደሰታል፤ እነዚህ ሰባቱ መቅረዞች ዓለምን የሚያካልሉ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናቸው።” #ራዕ. 5፥6።
11እኔም እንዲህ በማለት መልሼ ጠየቅሁት፦ “እነዚህስ በመቅረዙ ግራና ቀኝ የቆሙት የወይራ ዛፎች የምን ምሳሌዎች ናቸው? #ራዕ. 11፥4። 12የወይራው ዘይት ከሚፈስስባቸው ከሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ያሉትስ ሁለቱ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የምን ምሳሌዎች ናቸው?”
13እርሱም “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ፤ እኔም “ጌታዬ ሆይ! አላውቅም” አልኩት።
14እርሱም “እነዚህ እግዚአብሔር የቀባቸውና በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ቆመው የሚያገለግሉ ሁለቱ ሰዎች ናቸው” አለኝ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997