ወደ ቲቶ 3:1-8

ወደ ቲቶ 3:1-8 አማ05

ሰዎች ሁሉ ለገዢዎችና ለባለሥልጣኖች በትሕትና እንዲታዘዙ፥ መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁዎች እንዲሆኑ፥ በማንም ላይ ክፉ ነገር እንዳይናገሩ አሳስባቸው፤ ይልቅስ ከሰው ጋር የማይጣሉና ገሮች፥ ፍጹም ትሕትናን ለሰው ሁሉ የሚያሳዩ ይሁኑ፤ እኛም ከዚህ በፊት ሞኞች፥ የማንታዘዝ እምቢተኞች፥ መንገዳችንን የሳትን ተላላዎች፥ ለልዩ ልዩ ፍትወትና ሥጋዊ ደስታ የተገዛን፥ በተንኰልና በምቀኝነት የምንኖር፥ የተጠላንና እርስ በርሳችንም የምንጣላ ነበርን። ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ደግነትና ፍቅር የተመላ ርኅራኄ በተገለጠ ጊዜ፥ እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ራሱ በምሕረቱ አዳነን፤ ያዳነንም በአዲስ ልደት መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በተገኘው መታደስ ነው። እግዚአብሔር በለጋሥነቱ በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት መንፈሱን በብዛት አፈሰሰልን። ይህንንም ያደረገው በጸጋው ጸድቀን በተስፋ የምንጠባበቀውን የዘለዓለምን ሕይወት እንድንወርስ ነው። ይህ የታመነ አባባል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑ ሰዎች ለመልካም ሥራ እንዲተጉ ይህን ነገር ሁሉ በጥብቅ እንድታስገነዝብ እፈልጋለሁ፤ ይህም ነገር መልካምና ለእያንዳንዱ ሰው ጠቃሚ ነው።