ቲቶ 3:1-8
ቲቶ 3:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፥ ማንንም የማይሰድቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤
ቲቶ 3:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰዎች ለገዦችና ለባለሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው። እንዲሁም በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ አስገንዝባቸው። ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኛነት እንኖር ነበር። ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው። ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።
ቲቶ 3:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፥ ማንንም የማይሰድቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝንት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤
ቲቶ 3:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰዎች ሁሉ ለገዢዎችና ለባለሥልጣኖች በትሕትና እንዲታዘዙ፥ መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁዎች እንዲሆኑ፥ በማንም ላይ ክፉ ነገር እንዳይናገሩ አሳስባቸው፤ ይልቅስ ከሰው ጋር የማይጣሉና ገሮች፥ ፍጹም ትሕትናን ለሰው ሁሉ የሚያሳዩ ይሁኑ፤ እኛም ከዚህ በፊት ሞኞች፥ የማንታዘዝ እምቢተኞች፥ መንገዳችንን የሳትን ተላላዎች፥ ለልዩ ልዩ ፍትወትና ሥጋዊ ደስታ የተገዛን፥ በተንኰልና በምቀኝነት የምንኖር፥ የተጠላንና እርስ በርሳችንም የምንጣላ ነበርን። ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ደግነትና ፍቅር የተመላ ርኅራኄ በተገለጠ ጊዜ፥ እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ራሱ በምሕረቱ አዳነን፤ ያዳነንም በአዲስ ልደት መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በተገኘው መታደስ ነው። እግዚአብሔር በለጋሥነቱ በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት መንፈሱን በብዛት አፈሰሰልን። ይህንንም ያደረገው በጸጋው ጸድቀን በተስፋ የምንጠባበቀውን የዘለዓለምን ሕይወት እንድንወርስ ነው። ይህ የታመነ አባባል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑ ሰዎች ለመልካም ሥራ እንዲተጉ ይህን ነገር ሁሉ በጥብቅ እንድታስገነዝብ እፈልጋለሁ፤ ይህም ነገር መልካምና ለእያንዳንዱ ሰው ጠቃሚ ነው።
ቲቶ 3:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለገዢዎችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። እንዲሁም ማንንም የማይሰድቡ፥ ጠበኛ ያልሆኑ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ በጽኑ አስገንዝባቸው። እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባርያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት ጊዜያችንን የምናሳልፍ፥ የምንጠላ፥ እርስ በርሳችንም የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እኛ በጽድቅ በሠራናቸው ሥራዎች ሳይሆን እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እኛን አዳነን፤ ይህንንም መንፈስ፥ በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ በዚህም በጸጋው ጸድቀን በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች ለመሆን በቅተናል። ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲተጉ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤