በክርስቶስ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ኅሊናዬም እንደማልዋሽ ይመሰክርልኛል። ትልቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ፤ በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑት ወገኖቼ ስል እኔ ከክርስቶስ ተለይቼ የእግዚአብሔር ርግማን ቢደርስብኝ በወደድኩ ነበር። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ልጆቹ አደረጋቸው፤ ክብሩን ገለጠላቸው፤ ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ ሕግን ሰጣቸው፤ እውነተኛውን የአምልኮ ሥርዓት አሳያቸው፤ የተስፋውንም ቃል ሰጣቸው። እነርሱ በትውልዳቸው ከነገድ አባቶች የመጡ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የመጣው ከእነርሱ ዘር ነው፤ እርሱ ከሁሉ በላይ ነው፤ ለዘለዓለምም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን! ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ተሽሮአል ማለት አይደለም፤ የእስራኤል ዘር በሙሉ እውነተኞች እስራኤላውያን አይደሉም። እንዲሁም የአብርሃም ዘር ሁሉ የአብርሃም ልጆች ናቸው ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አብርሃምን “ዘር የሚወጣልህ በይስሐቅ ነው” ስላለው ነው፤ ስለዚህ በሥጋ የተወለዱት የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን ዘር ሆነው የሚቈጠሩት የተስፋው ቃል ልጆች ብቻ ናቸው። ይህም እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” የሚል ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ርብቃ የነገድ አባታችን ከሆነው ከይስሐቅ መንታ ልጆችን በፀነሰች ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ምርጫ በሥራ ሳይሆን በጥሪ መሆኑን ለመግለጥ ሁለቱ ልጆች ከመወለዳቸውና ክፉም ሆነ ደግ ከማድረጋቸው በፊት እግዚአብሔር ርብቃን “ታላቁ ለታናሹ ተገዢ ይሆናል” አላት። ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለትስ ከቶ አንችልም! እግዚአብሔር ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፥ ልራራለት የምፈልገውንም እራራለታለሁ” ብሎታል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምርጫ የሚገኘው በሰው ፈቃድና በሰው ሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት ነው። በዚህ ምክንያት በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ግብጽ ንጉሥ “በአንተ ኀይሌን ለማሳየትና ስሜም በዓለም ሁሉ ላይ እንዲታወቅ ለማድረግ አንተን አንግሼሃለሁ” የሚል ቃል ተጽፎአል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ይምረዋል፤ የሚፈልገውንም እልኸኛ ያደርገዋል። ስለዚህ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመቃወም ማንም አይችልም፤ ታዲያ፥ እርሱ ሰዎችን በክፉ ሥራቸው ለምን ይወቅሳቸዋል” ብለህ ትጠይቀኝ ይሆናል። አንተ ሰው! ከእግዚአብሔር ጋር ለመከራከር ምን መብት አለህ? የሸክላ ዕቃ ሠሪውን “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ሊለው ይችላልን? ሸክላ ሠሪ ከአንድ ዐይነት የሸክላ ጭቃ አንዱን ዕቃ ለክብር፥ ሌላውን ለተራ አገልግሎት አድርጎ ለመሥራት ሥልጣን የለውምን?
ወደ ሮም ሰዎች 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮም ሰዎች 9:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች